



በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ ቡዱኑን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ልዑክ ቡዱኑ መርተው የመጡት የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሜቴ አባል ዩዲ ሜርሴዲስ ኸርናንዴዝ ሲሆኑ የሁለቱን ሀገራት ለዘመናት የዘለቁ ቤተሰባዊነት የተላበሱ ግንኙነቶች የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርገዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ የኢትዮ-ኩባ ታሪካዊ ግንኙነት አውስተው በአሁኑ ግዜ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች እጅግ ውጤታማ ስኬቶች እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን፤ ምጣኔ ሀብቱ ባለፈው ዓመት በአማካይ በ8.1% ማደጉን በዚህ ዓመትም በ8.4% ለማሳደግ ታቅዶ እየሰራ እንደሆነ አንስተዋል።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት በአምስት ዘርፎች በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሆነ ያብራሩት ክቡር አቶ አደም በተለይም በግብርናው መስክ በተለይ በስንዴ ምርት እምርታዊ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሻለ ስራ ለማከናወን ትብብር እንደሚጠናከር ገልፀው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሜቴ አባል ዩዲ ሜርሴዲስ ኸርናንዴዝ በበኩላቸው በሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ፓርቲያቸው እንዲሳተፍ መጋበዙ ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል።
ሀገራቱ በኢንቨስቶመንት፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች መስኮች ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት በማጠናከር ሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ያላቸውን የጋራ ታሪክ የሚያጠናክር፣ ዕድገታቸውንም የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
