
ብልፅግና ፓርቲ ከበርካታ ተግዳሮቶች ጋር እየታገለ መጠነ ሰፊ ለውጦችን ማምጣቱን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሁለተኛውን የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
“ብልፅግና የሀሳብ ግልጽነት ያለው ፓርቲ እና ሀሳቡን ተግባራዊ በማድረግ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለውጦችን ማምጣት የቻለ ነው” ብለዋል፡፡
ፓርቲው በአንደኛው መደበኛ ጉባኤው ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ ቃል መግባቱን አስታውሰው፤ ቃሉን ተግባራዊ በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከማስቀረት አልፎ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ምርታማነት በጣም ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የውጭ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ገለልተኛ፣ ነጻ እና ብቁ ተቋማት እንዲፈጠሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን በማንሳት ምርጫ ቦርድ፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የፍትህ ተቋማት እና የፀጥታ ተቋማት በዚህ ረገድ ለውጥ እያሳዩ ያሉ ናቸው ብለዋል፡፡
የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት አዲስ አስተሳሰብ እንዲኖር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፖለቲካ እና ሌሎች የቆዩ ቅራኔዎች እንዲፈቱ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲው ስብራቶች አሉ ብሎ ስለሚያምን ያንን ለመቀየር እየሠራ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የተለያየ ስም እየተሰጣቸው እንዲሰደዱ የተደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮቻቸው ወደ ሀገር እንዲመለሱ የተደረገው በዚህ መሠረት ነው ብለዋል፡፡
በዲፕሎማሲው ረገድ የመጣው ለውጥ የግልጽ ፖሊሲ ውጤት እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ብሄራዊ ጥቅምን ባስከበር መልኩ ቅድሚያ ለጎረቤቶቻችን ሰጥተን መስራታችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ውጤማነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
ብልፅግና ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ለውጦች ቢመጡም ፅንፈኝነት፣ የሥራ ባህላችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች፣ ሌብነት እና ብልሹ አሠራር ፈተና መሆናቸውንም አንስተዋል።
በእነዚህ ክፍተቶች ላይም ጉባኤው ቁርጠኛ ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል ያሉት ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ እንደተለመደው ፈተናዎችን ወደ ዕድል ቀይሮ ለቀጣይ ስኬት ዝግጁ እንደሚሆን ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
