






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የተግባር አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ አካሂዷል ።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ የሺዋስ ዓለሙ የተቋሙን ተቀባይነትንና ውጤታማነት ለማጠናከር የአንድ ዕቅድ፣ በጀትና ሪፖርት ስርዓቱን በቀጣይ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አክለውም የተለያዩ የመንግስት መረጃዎችን በአግባቡ በማደራጀት፣ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ተከታዮችን ማፍራት የመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ማጠናከር ለዚሁም ብቃት ያለውን ሳቢ ይዘት መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል ።
ወቅታዊ አጀንዳዎችን ማድረስ፣ የመንግስት መግለጫዎች በየጊዜው መስጠት፣ ከባለድርሻ የሚዲያ ተቋማት ጋር መቀናጀት፣ የባለሙያዎችን አቅም በተግባር ማብቃትና ተቋማዊ አሠራርና ግንኙነት ማጠናከር በትኩረት መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል ።
የክልሉ ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለሙ ገብረ አፈጻጸምን በየጊዜው መገምገም የተሻለውን ለመሸለምም ሆነ ድክመቱን ለማሻሻል ወሳኝ በመሆኑ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር የየድርሻችንን በመውሰድ በህዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የክልሉን አንድነት ለማጠናከር፣ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የክልሉን አቅም ከፍ አድርገን ለማሳወቅ መስራት ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ በጥንካሬና በጉድለት የተነሱ ጉዳዮች በመናበብና በመቀናጀት ለቅሞ በመስራት ገዥ ትርክት በመገንባት የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ መኩሪያ ናቸው።
የመንግስት መረጃዎችን በአግባቡ በማደራጀት ተገቢውን መረጃ ከአንድ ምንጭ በመስጠት የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም በመንግስትና ህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ማገልገል እንደሚገባ የገለጹት የክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ም/ኃላፊና የመንግስት መረጃ አስተዳደርና የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት መስፍን ወዳጆ (ዶ/ር) ናቸው።
የክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ም/ኃላፊና የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ የህዝብ አስተያየትን በጥራትና በፍጥነት በማሰባሰብ ወደ መንግስት በማድረስ፣ በመንግስት ምላሽ የተሰጡ ጉዳዮችን በተለያዩ ሚዲያዎች አጀንዳ በመስጠት፣ በማቀናጀትና በመጠቀም ወደ ህዝብ በማድረስ ላይ ትኩረት እንጀሚሻ ገልጸዋል ።
የ2017 ዓ/ም የስድስት ወር የተግባር አፈጻጸም በተቋሙ ዕቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ መልካሙ ኃ/ማሪያም ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል ።
ተሳታፊዎቹ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን በማንሳት የተናበበ ዕቅድ እስከታችኛው መዋቅር መውረዱ፣ በተቋሙ የሰው ኃይል ለማሟላት ጥረት መደረጉ፣ በጀትን ለታለመለት ዓላማ ማዋል፣ በማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ተጨማሪና ሳቢ ይዘቶችን መጠቀምና ተከታይን ከማፍራት ፣ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች እየሰፉ መምጣት፣ የተለያዩ የመንግስት መረጃ መደራጀቱ፣
በሚዲያና ህዝብ ግንኙነት የህትመት ውጤቶች እያደጉ መምጣት፣ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ቅንጅታዊ ስራ እየተሻሻለ መምጣት፣ የተለያዩ ኩነቶችና ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱ፣ የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት መዘርጋት፣ በተለያዩ ሀገራዊና ክልላዊ ገዳዮች ላይ ለህዝብ መግለጫዎች መሰጠቱ፣ ወቅታዊ አጀንዳዎች እየተቀረጹ በየጊዜው መሰጠቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከሁሉም የክልሉ መዋቅር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮች፣ የዞን የወረዳና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጌታሁን ግርማ
