ወቅታዊና ተአማኒነት ያለውን መረጃ ለህብረተሰቡ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ገለፁ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከየሚዲያና ሥር መዋቅር ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም በቦንጋ ከተማ ገምግሟል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በህዝብና በመንግሥት መካከል ቀልጣፋ የመረጃ ተደራሽነት እንዲኖር ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ በየጊዜው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በመከታተል ተደራሽ ከማድረግ ረገድ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች የህዝብን አንድነት፣ አብሮት የሚያጠናክሩና አንድ የሚያደርጉ ካፋፋይ ያልሆኑ የህዝቦችን አብሮት ይበልጥ ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ አጀንዳዎችን በማሰራጨት ትልቅ ሚና እየተወጡ ያሉ ተቋማት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እጅግ ተስፋ የሚሰጡ፣ ክልሉም ያለውን አቅም በሚገባ ማስተዋወቅ የሚችል አቅም የፈጠርንበት ነው ያሉት፡፡

በየዞኖቹ ከዚህ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ትኩረት ከሚደረገው በመላቀቅ በተለያዩ ህትመትና ብሮዲካስት ሚዲያዎችም ጭምር ሰፊና ወጤታማ ስራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የሚቀርቡ መረጃዎች እውነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሙያን መሰረት አድርገው ለህብረተሰቡ ለመቅረብ የባለሙያዎችን የክህሎት እና የእውቀት ክፍታት ለመሙላት ተከታታይ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠና በየጊዜው መሰጠት እንዳለበት አስረድተዋል።

የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና የሚዲያ ተቋማት አመራሮች የግንኙነት አግባብን በየጊዜው ማጠናከር የተደራጀ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ነው ያመላከቱት ተሳታፊዎቹ በታችኞቹ የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሮች ከሰው ሃይል፣ ከበጀት እና ወጥ የሆነ መዋቅር ያለመኖር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች መፍታት፤የቢሮው ድጋፍ፣ ክትትልና ግብረመልስ የመስጠት ሂደቱ ሊጠንከር እንደለበትም ጠይቀዋል፡፡

የአፈፃፀም ግምገማው ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ትልቅ አቅም የሚሆን እና ለቀጣይ ስራ መነሳሳት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመግባባት እና ቅንጅታዊ አሰራርን በመከተል ወቅታዊና ታአማኒነት ያለውን መረጃ ለህብረተሰቡ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *