«የሜኔ ሻዴ ባሮ» የመቻቻል እና የአብሮነት እሴት ማሳያ::

Spread the love

የካፈቾ ብሄር ከጥንት ጀምሮ የራሱ የቀን አቆጣጠር ያለው ሲሆን «የሜኔ ሻዴ ባሮ» በብሄሩ ዘንድ ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲሱ መሸጋገርያ ነው።

ታላላቅ የብሔሩ ተወላጆችም ከጥንት ጀምሮ በራሱ ስርአትና ወግ ለትውልድ ሲተላለፍ መቆየቱን ያወሳሉ። በዓሉ ዘመን የሚለወጥበት፣ ከአሮጌው ወደ አዲስ የሚታለፍበት፣ ወቅት ስለመቀየሩ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ከመከበሩ ባሻገር አያሌ ትርጉም ያላቸው ተግባራት የሚከናወኑበት ነው።

የነፃነት ማሳያ ተደርጎ የሚቆጠርበት አውድም ያለው ነው። በመላው ዓለም በሚባል ሁኔታ ሴቶች በጥንት ዘመን በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ተሳትፎና ሚና እኩል ተደርገው የማይታዩበት ስርአት የበረታበት ነበር።

«የሜኔ ሻዴ ባሮ» ከተለያዩ አካባቢዎች፣ በፆታ፣ በሀይማኖት፣ በእድሜ ወዘተ ሳይገደቡ ሁሉም በአደባባይ ወይም ለበዓሉ የብሔሩ መሪዎችና ህዝብ ተስማምተው በመረጡት ስፍራ ያከብራሉ። ሴቶች በባህላዊ ልብሶቻቸው ደምቀውና ተውበው እኩል ያከብሩታል። “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” ይሉት ብሒል በዚህ በዓል ይሻርና እኩልነት ቦታና ጊዜ ይሰጠዋል።

አብሮነት ደግሞ የበዓሉ ትልቁ እሴት ሆኖ የሚታይበትና ለአከባበር ስርአቱ የተለየ ውበት የሚሰጠው ነው። የተቸገሩ ወገናቸውን ተማምነው እኩል በልተው ጠጥተው፣ ከፊታቸው ላይ ፈገግታ የሚታይበት የሰው ልጅን ህብረትና ወዳጅነት አድምቆ የሚያሳይ በዓል ነው «የሜኔ ሻዴ ባሮ»።

በዓሉም ከአዝመራ ወቅት ጋር ቁርኝት ያለው ሲሆን በራሱ የቀን አቆጣጠር የመጀሪያዉ የአዝመራ ወቅት መጠናቀቁን ተከትሎ በድምቀት ይከበራል።

በዚህ በዓል ከሚያሸልሙ ተግባራት መካከል ለተፈጥሮ ደህንነት ጠንክሮ መስራት ዋነኛው ነው። የአብሮነት እሴቶች ደምቀው የሚታዩበት እንዲሁም ለሀገርና ለወገን መልካም የሰራ እውቅና ተሰጥቶት ያጎደለ የሚነቀፍበትና የሚመከርበት ነው። በዚህ በዓል ዓመቱን ሙሉ የተከናወኑ ህዝባዊ፣ ግለሰባዊና መንግስታዊ ስራዎች የሚፈተሹበት ነው።

ካፈቾዎች ከጥንት ጀምሮ በጠንካራ ስርወ-መንግስታት የተዳደሩ ሲሆን “ሚንጆ” የመጨረሻው ስርወ-መንግስት ነው። የዚህ ስርወ-መንግስት የመጨረሻው ንጉስም ታቴኖ ጋኪ ሻሮች ይባላሉ።

«የሜኔ ሻዴ ባሮ» በንጉስ ጋካ ሻሮቺ ጊዜ አና ከዚያም በፊት በካፋ ህዝብ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት አንዱና ዋነኛው ነው።

ይህ በዓል በዚያን ዘመን የነበሩ መንግስታት በዓል እንደነበር ይነገራል። ንጉሳዊ አስተዳደሩም በምክር ቤት አባላት የሚመራ ሲሆን ይህም ለአሁኑ ዘመናዊ አስተዳደር መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል።

የምክር ቤት አባላቱም ጉጄራሾ (ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ ካታሜራሾ (የከተማና የጦር ሚኒስትር)፣ አዋራሾ (ፍትህ እና ፍርድ ሚኒስትር)፣ ሾደራሾ (የህዝብ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ አርቸራሾ (የማስታወቂያ ሚኒስትር)፣ አዲዬራሾ (የቤተ-መንግስትና የንጉሱ ጥበቃ ሚኒስትር)፣ ቦደራሾ (የስራ ሚኒስትር) – ቦደራሾ ብሔሩ ካፋ ቢሆንም ባይሆንም በአካባቢው የተወለደ እስከሆነ ድረስ ይሾማል። ትንሽ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ተወካዮች እንዲካተቱ በመታሰቡ የሚሾም ነው።

ከእነኚህ ባሻገር ሌሎች የምክሬቾ(የምክር ቤት አባላት) እንደየደረጃቸው ተግባራትን ይከውናሉ። ከላይ ከጠቀስናቸው ሰባት የምክር ቤት አባላት በተጨማሪ ዎፋራሾ (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢንቨስትመንትና የሀብት ሚኒስትር)፣ ቡንደራሾ (የገንዘብ ሚኒስትርና ረዳት ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ ናንጋራሾ (የንግድ ሚኒስትር)፣ ሪበራሻ (የገቢዎች ሚኒስትር)፣ ሆነው በምክር ቤት አባልነት የተካተቱበት የአስተዳደር ስርአት ነበር።

በተለይም ንጉሱ እጅግ የሚከበሩ፣ በማህበረሰቡ የሚወደዱ እና መንፈሳዊ መሪም ተደርገው የሚቆጠሩ ስለሆኑ በብዙ ስራዎች እንዲደክሙ አይፈለግም። ስለዚህም አብዛኞቹን የአስተዳደር ስራዎች የሚከውኑት ጉጀራሾ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ትዕዛዞችን ማስተላለፍና ስራዎችን መገምገም ግን የንጉሱ ተግባር ነው።

በዓሉ ከአዝመራ ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ ሊከበር 77 ቀናት ሲቀሩት ህዝቡ የአዲስ ዘመን መለወጫ ብሎ ሃምሌ አንድ አዝመራውን ይጀምራል።

የአዝመራ ወቅት ሊያበቃ 25 ቀናት ሲቀሩት “ካሼ ዋጦ” የሚባል ስርአት ገቢራዊ ይሆናል። ይህ ማለት፤ ሞፈርና ቀንበር እንዲሁም እርፍና ማረሻ ተለያይተው፣ አዝመራውን ሁሉ ከገበሬው እኩል ሲደክሙ የከረሙ በሬዎች እረፍት የሚያገኙበት ነው።

ካፈቾዎች ለእንስሶቻቸው ጭምር የሚሳሱ ስለመሆናቸው አንዱ ማሳያ በእርሻ የደከሙ በሬዎቻቸውን በዚህ ወቅት አብዝተው መንከባከባቸው ነው። የምስጋና እንጉርጉሮዎችም በዘመን መለወጫ በዓላቸው ሰሞን በስፋት ይደመጣሉ። ገበሬው ለእርሱም ለበሬውም የእረፍት ጊዜ ነውና በዘፈን በሬውን እያመሰገነ፣ “ከሁሉ ሰው እኩል በዓል የማከብረው፣ ልጆቼ ያልተራቡብኝ፣ ቤተሰቤ በደስታ ከዓመት ዓመት የሚሸጋገረው ባንተ ነውና አመሰግናለሁ” እያለ ያንጎራጉራል። ለበሬው ካመረተው ሁሉ በአይነት በአይነት እያቀላቀለ ይመግበዋል። አንድም ለውለታው ምስጋና፤ ሁለትም ለቀጣይ አዝመራው ጉልበቱ ጠንክሮለት እንዲዘጋጅ።

በዓሉም የንጉሱ መቀመጫ በሆነው «ቦንጌ ሻምበቶ» የሚከበር ሲሆን በዚህ ወቅት «የዎራፌ ራሾዎች» ስራም ይገመገማል። «ዎራፌ ራሾ» ማለት የግዛት አስተዳዳሪ ሲሆን በአሁኑ የሀገራችን አስተዳደር ስርአት የክልል አስተዳዳሪዎች እንደ ማለት ነው። ከግምገማዎቹ መካከል ከሌሎች አካባቢዎች ከመጡ ሰዎች ጋር ተስማምቶ የመኖርና የመከባበር ዝንባሌ አንዱ ነው። በዚህም ያጠፋ ይቀጣል የተሻለም ይሸለማል።

በሌላ በኩል ማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ባህሉ በትኩረት ይገመገማል። በአሁን ወቅት ካፋ አካባቢ እጅግ ለኑሮ ተስማሚ የአየር ሁኔታ በዚያ ጠንካራ ስርአት አማካኝነት የተገኘ ነው ተብሎ ይታመናል። የአካባቢው ጥቅጥቅ ደን አስከዛሬ እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገውም ይኸው ባህልና ስርአት ለመሆኑ የዛሬው አረንጓዴ ምድር የሚመሰክር ይመስላል።

የካፈቾ ዘመን መለወጫ በዓል «የሜኔ ሻዴ ባሮ» በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህል፣ የትምህርትና የሳይንስ ተቋም (UNESCO) እንዲመዘገብ እና ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውበቶች አንዱ ሆኖ ዓለም እንዲያውቀው ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ ዝግጅት እየተደረገ ነው መባሉን የዘገበው ደሬቴድ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *