












ፋና ወጊው “የእሞታ” አዳሪ ትምህርት ቤት
ኮንታ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ከሚገኙ ስድስት ዞኖች አንዱ ነው ። ዞኑ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ለም መሬት፣ ቱባ ባህልና የቱርስት መዳረሻዎች ያሉበት ለዓይን የሚማረክ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እና በገበታ ለሀገር የተሰራ የዝሆን ዳና ሎጅን ባለቤት መሆኑን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል ።
በዞኑ ውስጥ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ብዙ ተሰፋ ሰጪ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ፤ አመርቂ ውጤትም እየተመዘገበ ነው።
ከነዚህም የማህበራዊ ልማት አንዱና ዋነኛው የትምህርት ዘርፍ ስራ ነው። በዘረፉ የትምህርት ብክነት በመቀነስና ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ አካባቢ በመፍጠር የተማሪ ውጤት በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብሎም በሀገር ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ሰፊ ተግባራት እየተሰራ ይገኛል ።
በዛሬው ቆይታችን ከነዚህም አንዱ የሆነውና በዘርፉ የተጣለውን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው “የእሞታ አዳሪ ትምህርት ቤትን” ለመቃኘት እንሞክራለን ።
የአዳሪ ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት ከማስጠበቅ ያለው ፋይዳ፦ ልጆች በተለያዩ የህይወት መስኮች እንዲያድጉ፣ በትምህርት ስርዓቱ እና በማህበረሰቡ ውስጥ የተሟላ ስብዕና ያለ ሰው ሆኖ እንዲያድጉ እጅግ አስፈላጊ ነው።
የእሞታ ት/ቤት በ2016 ዓ/ም የተለያዩ የአሠራርና አደረጃጀት መመሪያ በማዘጋጀት በ8ኛ ክልላዊ ፈተና 60% እና ከዛ በላይ ያመጡ እንዲሁም በ7ኛ እና 8ኛ የክፍል ትምህርት ከ80 እና ከዚያ በላይ፣ በእንግሊዘኛና ሒሳብ ትምህርቶች 80 እና በላይ ያመጡ ተማሪዎችን በመመልመል የመግቢያ ፈተና በመስጠትና በመግቢያ ፈተናው 80 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመቀበል የተጀመረ መሆኑን የት/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን ሰበቦ ተናግረዋል ።
ት/ቤቱ ስራ ስጀምር በ50 ተማሪዎች የጀመረና ሁለቱ በማህበራዊ ምክንያት ከት/ቤት የወጡ ከ48 ውስጥ 13 ተማሪዎች በዓመቱ መጨረሻ ከ80 በታች በማምጣታቸው መስፈርቱን ሳያሟሉ በመቅረታቸው ከት/ቤት በመውጣታቸው አሁን 35 ተማሪዎች በ10ኛ ክፍል እና 44 በ9ኛ በድምሩ 79 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
በት/ቤቱ የተሻለ ስነምግባር ያላቸውና የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉ 13 የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መ/ራን ማስታወቂያ በማውጣት በውድድር ገብተው በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ፤ የ20 የአስተዳደር ሰራተኞች የትምህርት ጥራት ለማምጣት በተለያየ ዘርፎች ዕገዛ ከማድረጋቸውም በላይ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን አብራርተዋል ።
የት/ቤቱ ወጪ ሙሉ በሙሉ በኮንታ ልማት ማህበር የሚሸፍን ቢሆንም የዞኑ አስተዳደር በቅርበት በልዩ ሁኔታ የሚከታተል፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን አቶ ተስፋሁን አንስተዋል።
የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የመ/ራንን ሞራልና ጥቅማጥቅም ከማስበር አንጻር 2500 ብር አቻቸው ከሚያገኙት ደመወዝ ላይ ተጨማሪ መከፈሉ፣ የመኖሪያ ቤት ውሁና መብራት ወጪዎች በልማት ማህበሩ ተሸፍኖላቸው ሙሉ ጊዜውን ግቢ ውስጥ መሆናቸውን ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል ።
በተጨማሪም የተማሪውን ውጤት ለማሻሻልና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት አሰጣጥ ቀን ሙሉ መሆን፣ በሳምንት ሁለት ቀን የቱቶሪያል ክፍለ ጊዜ መዘጋጀቱና ማታ ቅዳሜና እሁድ ተጨማሪ ትምህርት መሠጠት፣ የፈተና ስርዓት ( Continues Assessment) ፣ ሚድና ማጠቃለያ ፈተና መስጠት፣ ይዘቱን ለመሸፈን ሰፋ ያሉ ጥያቄዎችን ማዘጋጀትና የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ በተቀመጠ ጊዜ መጀመር እንደ ተሞክሮ ተነስተዋል ።
የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን በተመለከተ የውሀ መስመር ስበላሽ በፍጥነት መድረስ፣ የግቢውን ውስጥ ለውስጥ መንገድ የዞኑ መንግስት የሳሊን ድርጅትን በማስተባበር መሰራቱንና ሌሎች ተጠቅሰዋል ።
ትምህር ቤቶች ከዕውቀት ግብይት ማዕከልነት ባሻገር የሰርቶ ማሳያ፣ የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ከማድረግ እንዲሁም የገቢ ምንጭን በማሳደግ የትምህርት ግብዓትን ከማሟላትና በግቢ የሚኖሩ ተማሪዎች ምገባ ለመሸፈን የተለያዩ የጓሮ አትክልት፣ አምስት የወተት ላሞችን በመግዛትና ወደ 230 ዶሮዎችን እርባታ መጀመሩ ተገልጿል ።
ይሁን እንጂ ት/ት ቤቱ አዲሱ በመሆኑ የት/ቤቱን መሠረተ ልማት ለማሟላትና የተማሪዎች መዝናኛ ከማመቻቸት እና የተማሪውን ወጪ ከመሸፈን ቁጥሩ እየጨመረ ስለሚመጣ የህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል ።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መ/ር ያዕቆብ ከተለ የት/ቤቱ የመከፈት ዓላማ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል እየቀነሰ የመጣውን የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ ተወዳዳሪ ዜጋን በማፍራት ሀገርቱ ሁለንተናዊ ዕደገት ሚናውን መጫወት እንደሆነ ተናግረዋል ።
ትምህርት ቤቱ ከሌላው የሚለየው ተማሪዎችም ሆነ መ/ራን በውድድር የተሻለ ውጤት ያመጡ ተፈትኖ የገቡ መሆኑ፣ ከገቡ ተማሪዎች መካከል አቅማቸውን በተለያዩ የምዘና ዘዴ በመለየት ደከም ለሚሉት ልዩ ድጋፍ እንደምደረግ፣ ማታን ጨምሮ ቅዳሜና እሁደ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ፣የተለያዩ የፈተና ጥያቄዎችን በመስራት ማለማመድ ፣ በተደራጀው ዲጂታል የኮምፒውተር ላብራቶሪ ተማሪዎች በክፍል የተማሩትን በተግባር መለማመዳቸው የታለመውን ዓላማ ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል ።
ሀብትን በማፍራት ለመማር ማስተማር የሚሆኑ ግብዓቶችን ከማሟላት በላይ ለተማሪዎች ምገባ ወደ ወጪ የሚወጣውን ወጪ በራስ ለመሸፈን የጓሮ አትክልት፣ 230 የዶሮና 5 የወተት ላም እርባታ መጀመሩን በቀጣይ ምገባውን ከግቢ ለመሸፈን ጥረት እየተረገ መሆኑን ማሳያ መሆኑን ርዕሰ መ/ሩ አንስተዋል ።
በቀጣይ ት/ቤቱ 12ኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል 75% ተማሪዎች ከሚፈተናቸው የት/ት ዓይነቶች ውጤቱን 75% እና ከዚያ በላይ ማስመጣት ፣ ሁሉም ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት፣ ከተፈተኑት 50% ተማሪ የውጪ ስኮላር እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅደው እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል ።
የት/ቤቱ ርዕሰ መ/ር በተደራጀ ላብራቶሪ ግብዓት ያለመሟላት፣ የተለያዩ የማጣቀሻ መጽሐፍ እጥረትና የራሱ የሆነ የውሃ መስመር በግቢ ውስጥ ከመዘርጋት በቀጣይ መሻሻል እንዳለበት ጠቁመዋል ፤ለመ/ራን የሙያ ማሻሻያና አቅም ግንባታ ስልጠና፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጨምረው አንስተዋል ።
ተማሪ ረድኤት ታደለ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ውስን ተማሪዎች በተመረጡ መ/ራን በተሻለ ቦታ ቀን ሙሉ መማር ለት/ት ጥራት ፋይዳው የጎላ መሆኑንና ተማሪዎች አብሮ ተቻለው የመኖርን ባህልን ከወዲሁ የሚለማመዱበት እንደሆነ ገልጻለች ።
ተማሪ ሳሙኤል አስራት 10ኛ ክፍል ተማሪ በበኩሉ ወደ ት/ት ቤቱ ስመጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ከሚያስመዘግቡት ተማሪዎች አንዱ ለመሆን በማሰብ እንደሆነና ትምህርት ቀን ሙሉ መሰጠቱና የተለያዩ፣ መለማመጃ ጥያቄዎች በመ/ራን መሠራቱና ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ጠይቀው ለመረዳት ተማሪና መ/ሩ በአንድ ግቢ መሆኑ ከሌሎቹ ት/ቤቶች በተለየ መልክ ለመዘጋጀት እንደሚያግዝ አንስተው በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የውጭ ስኮላር ለማግኘት እንደሚያጠና ተናግሯል ።
ተማሪ ሬድኤት ጥላሁን 9ኛ ክፍል ተማሪ ከሩቅ ለሚመጡና ምቹ የማንበቢያ ስፍራ ለሌላቸው ተማሪዎች ርቀትና ዕንግልት በመቀነስ ምቹ አካባቢ እንደፈጠረላቸው ፣ የትምህርት አሰጣጡ ከንድፈ ሀሳብ በላይ በተግባር ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስታ በቀጣይ ከ500 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ለማጥናት ማቀዷን አንስተዋለች።
እኛም በትምህርት ቤት ተዟዙረን የተመለከትናቸውና የአዳሪ ትምህርት ቤት ለተማሪው ምቹ የመማሪያ አካባቢ በመፍጠር የት/ቤት ምገባ ባህልና አብሮ የመኖር ባህልን ከማሳደግና በተማሪዎች መካከል የውድድር መንፈስ በመፍጠር፣ በራስ መተማመንን በመጨምር የተማርሪዎች ውጤትን ከማሻሻልም በላይ ብቁ ዜጋን ከማፍራት በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ መጠናከርና መስፋፋት እንደሚገባ በመጠቆም የዛሬውን በዚሁ አበቃን።
በጌታሁን ግርማ
