







ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ባከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት 397 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የዘንድሮው ምረቃ ለ5ኛ ጊዜ የተከናወነ ሲሆን በመርሃ-ግብሩ ከመደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ የማታ ፣ የሳምንቱ መጨረሻ እንዲሁም የክረምት ተማሪዎችም ተካተዋል።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዼጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ ባስተላለፉት መልእክት የዛሬውን ሳይጨምር ባለፉት አራት ምረቃዎች ከ4000 በላይ ተማሪዎችን አስመርቀናል ያሉ ሰሆን በተለይ የዛሬው የጤና ሳይንስና የካፊኖኖ ትምህርት ክፍል ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ተመራቂ እንደመሆናችሁ የተቋማችን እድገት መሰላል ማሳያዎች ናችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ራስ አገዝ ለመሆን እያከናወነ ያለውን በርካታ ተግባራት የዘረዘሩ ሲሆን ተቋሙ ያለውን አለም ዓቀፋዊ ግንኙነትም ጠቅሰዋል ።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ዋና ረጅስትራር ዶ/ር በሀይሉ ገ/ማሪያም ተመራቂዎችን በየኮሌጆቻቸው ዲኖች በኩል አቅርበው መመረቃቸውን አብስረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕ/ር ክፍሌ ወ/ሚካኤል ለተመራቂዎች ባስተላለፉት ቁልፍ መልእክት የዛሬ ተመራቂዎች ታሪካዊ ናችሁ ብለው ዘር ፣ ቀለም ፣ጎሳና ብሄር ሳትለዩ ሞያዊ ስነ-ምግባርን መሰረት ባደረገ መልኩ ሕዝባችሁን አገልግሉ እንዲሁም ት/ት የሚቆም ባለመሆኑ ለለውጥና ለተሻለ ነገር መትጋት ይገበ ባችኋል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት በተለይ በጤናው ዘርፍ ለተመረቁ ምሩቃን ችግሮችን ወደ እድል በመቀየር ሞያዊ ታማኝነታችሁን በመወጣት ማህበራዊ ብልጽግናን በጤናው ዘርፍ እንድታረጋግጡ በማለት የአደራ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲውና ከማህበረሰቡ ያገኛችሁትን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የመኖርን ጥበብ በሚትሄዱበት ሁሉ ሊትተገብሩት ይገባል ብለው መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው በመግለጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በመጨረሻም በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ተከናውኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር በጋራ በመዘመር የመርሃ-ግብሩ ፍፃሜ ማግኘቱን ከዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሚዲያ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል::
