




ከሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ በሁለተኛው የፓርቲው ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ በሰፊው መክሯል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በስልጣን ዘመናቸው ሁለት ጊዜ ወደ ዞናችን በመምጣትና ሁለት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ በማስገባታቸው እናመሰግናለን ብለዋል። የቤንች ሸኮ ዞን የወርቅ ክምችት ያለበት ፣ ለኤክስፖርት የሚሆኑ ቡና ፣ ቅመማ ቅመምና ሰብሎች የሚመረቱባት ዞን ናት ብለዋል።
የዞኑ መንግስትና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ባለፉት አመታት የሀይማኖት ተቋማት የመካነ መቃብርና መሰል ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ሚዛን አማን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የንግድ ፣ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል መሆኗን ጠቁመው የከተማዋ የኮሪደር ልማት ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የወደብ ጉዳይ የሀገራችን የዲፕሎማሲ ስራ ውጤት ስኬት መሆኑን የገለፁት የመድረኩ ተሳታፊዎች መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉ ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም የሚዛን አማን ማስተማሪያ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ፣ የሚዛን አማን ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እጥረት ፣ የኑሮ ውድነትና ሰው ሰራሽ የዋጋ መናር ፣ የውስጥ ለውስጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ መንግስትና ፓርቲው በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል አቶ በላይ ተሰማ መንግስና ፓርቲው በጥንካሬ የተነሱትን ወስዶ ማስቀጠልና ውስንነቶችን ፈጥኖ ማረም ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና ቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው ብልጽግና ወንድማማችነትና ህብረ ብሔራዊነትን ለማጽናት እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በዞኑ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁሌም ምኞታችንና ስራችን የዞኑን ህዝቡ በሁሉም የልማት መስኮች ተጠቃሚ ማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የአፋር ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ አህመድ እንደተናገሩት ብልጽግና ዕዳም ምንዳንም ተረክቦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የእኩልነት ፣ የልማት ተጠቃሚነት ፣ የዲሞክራሲ እና መሰል የህዝቡ ጥያቄዎችን ፓርቲው በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል። ፓርቲው ህልሞቹን በተጨባጭ ወደ እሳቤና እቅድ አውርዶ በመስራት ውጤት አስመዝግበናል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ታደሰ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ብልጽግና እሳቤያችን ፣ ዕቅዳችንና ስራችን ሁሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጽናትና ማበልጸግ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በየከተሞች የሚታዩ የመልካም አስተዳደሮችን ችግሮችን መለየት ፣ ማቀድና ደረጃ በደረጃ መፍታት ያስፈልጋል አቶ ይርጋ። ትውልድ ላይ መስራት ፣ ሰላምን ማጽናት ፣ ከተሞችን ውብ ፣ ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል ስሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
