




በቦንጋ ከተማ ሀገር አቀፍ የሕዝብ ኮንፈረንስ ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በህዝባዊ ውይይቱም በጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን በኩል በብልጽግና ፓርቲ 2ኛው መደበኛ ጉባኤ የተቀመጡ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
የኮንፈረንሱ መድረክ ተሳታፊዎች፤ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በቦንጋ ከተማ የተጀመሩ አዳዲስ የልማት ኢንሼቲቦችና ሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።
በከተማው የተጀመረው የኮረደር ልማት ሥራዎች ተሰፋ ሰጪ በመሆኑ የበለጠ እንዲጠናከር ያነሱት ተሳታፊዎቹ የቦንጋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፣የድሪ -ማሻ አስፓልት ፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ፓርቲው በትኩረት እንዲሰራ በአጽንኦት ጠይቀዋል።
በአከባቢው ያለው እምቅ ሀብቶችን ወደ ውጤት መቀየር እንዲቻል የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲቋቋም ያነሱት ተሳታፊዎች የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዝየም ጉዳይም ትኩረት እንዲሰጥበትም አንስተዋል።
ፓርቲው በመደበኛው ጉባኤ ያስተላለፋቸው እቅዶች የሀገሪቱን ብልጽግና የሚያሻግሩ እና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማረጋገጥ አጋዥ በመሆናቸው ለተፈጻሚነቱ በጋራ እንደሚተጉ ተሳታፊዎች በሀሳባቸው አረጋግጠዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
አቶ አወሉ አብዲ በመድረኩ እንደገለጹት፣ እንደሀገር ፓርቲው የህዝቡ መሠረታዊ ጥያቄ የሆኑ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ የጀመራቸውን ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ብልጽግና ፓርቲ ሀሳቦችን ሰንዶና አቅዶ ወደ ተግባር በመግባት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚሰራ መሆኑን በመሆኑ ከከተማው ህዝብ የተነሱ የልማት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው በመሆናቸው ፓርቲው ምላሽ ለመስጠት በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው አቶ አወሉ የጠቀሱት።
በፓርቲው መሪነት በከተማው የተጀመሩ የሰላም፣ሌማት ትሩፋት፣የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣የበጎ አገልግሎት እና ሌሎች ሥራዎች ግቡን እንዲመታ ህዝቡ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ የምክር ቤት አባል አቶ ፍቅሬ አማን ብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በፓርቲው የተጀመሩ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴት እንዲጠናከር ህብረብሔራዊ ገዥ ትርክት ለመገንባት እና ለማስረጽ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።
በቦንጋ ከተማ ከህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ያሉ እምቅ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም ህዝብን በማስተባበር የስራ ባህል በመቀየር የሚሰራ ይሆናል ብለዋል አቶ ፍቅሬ አማን ።
በፍቅር ከበደ
