




የሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና በቀሪ ወራት ትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ በማሻ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ገቢ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን ለማሳካት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀው ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 74 በመቶ እንዲሁም መደበኛ ገቢ 81 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
ካለን የገቢ አቅም አንፃር ስታይ አፈፃፀማችን ዝቅተኛ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ሁሉንም የገቢ አርዕስቶች ለይቶ በአግባቡ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ መረባረብ አለብን ብለዋል።
በዞናችን ያሉትን ሃብቶች እና ፀጋዎችን ተጠቅመን የተሻለ ገቢ በመሰብሰብ የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት በትጋት መስራት እንደሚገባ አቶ አበበ አሳስበዋል።
የሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተግባሩ እንደሻው በበኩላቸው ገቢ በተገቢው ከተሰበሰበ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እና ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
አክለውም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲረጋገጥ እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ገቢን መሰብሰብ ሚናው የጎላ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በጥንካሬ የተመዘገቡትን በማጠናከርና በጉድለት የተመዘገቡትን ለማሻሻል የየበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የገጠር መሬት መጠቀሚያ ፣የደረጃ ሽግግር ፣ቀጥታ የታክስ ገቢ፣ በግብይት ወቅት ደረሰኝ ያለመስጠትና ጠይቆ ያለመቀበል፣የማዘጋጃ ገቢ አፈፃፀም ዝቅተኛ በመሆኑ ፈጥኖ ማረምን ይጠይቃል ሲሉ ገልፀዋል።
የመምሪያው የ6 ወራት የገቢ አፈፃፀም ሪፖርት የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ተግባሩ እንዳሻው እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ሰፊ ውይይት ተደርጎ በቀጣይ ተግባራት ዙሪያ የስራ መመሪያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፣የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው ጀመሬን ጨምሮ የከተማ ከንቲባዎች፣የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
