




የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሚዛን ቅርንጫፍ ጣቢያ የ2017 የመጀመሪያ ግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም መድረክ በሚዛን አማን ተካሂዷል።
የቅርንጫፍ ጣቢያው የልማት ዕቅድና በጀት አስተዳደር ባለሙያ አቶ መካሻው ከበደ ባቀረቡት የ6 ወራት ሪፖርት ጣቢያው በቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞን በሚገኙ 5 ቋንቋዎች የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በግማሽ ዓመቱ በሬዲዮ ኬዝ 5ሺ 210 የሬዲዮ ዜናዎች ፣ 922 የሬዲዮ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ለአየር መብቃቱን ገልጸዋል። በቴሌቪዥን ኬዝ 131 የቴሌቪዥን ዜናዎችና 20 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ተቋሙ አዳዲስ የአቀራረብ ቢጋሮችን በመጠቀም የህዝብ ቅሬታዎችን በቀጥታ ስርጭት አድማጮችንና የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት ችግሮች እንዲፈቱ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በተለይም በትራንስፖርት አጠቃቀም ፣ በከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ፣ የሚዛን አማን የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ፣ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቲቺንግ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ዙሪያ ሰፊ ሽፋን መሰጠቱን ገልጸዋል።
የመድረኩ የተሳተፉ የጣቢያው ሰራተኞች እንደተናገሩት የስርጭት ተደራሽነት ችግር ፣ የማሰራጫ ጣቢያው የተከላ ስራ አለመጠናቀቅ ፣ የግብዓት አለመሟላትና ያሉትም ቢሮ ያረጁና አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውን እንደ እጥረት አንስተዋል። ከጥራት ፣ ተደራሽነትና የበጀት እጥረቱ ከተፈታ ተደማጭ እንሆናለን ብለዋል። በቅርቡም የቢጋር ለውጥ ከተደረገ በኀላም ጥሩ መነቃቃትና አድማጮችን እያገኘን ነው ብለዋል።
የጣቢያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ እንደተናገሩት በመድረኩ ለቀጣይ አቅም የሚሆንና ውጤታማ ሀሳቦች ተነስተዋል ብለዋል። የተቋሙን አደረጃጀት ማዘመንና በባለሙያ ማደራጀት ያስፈልጋል ብለዋል። የተቋሙን ውስን በጀት ለታለመለት አላማ ማዋልና ለውጥ ማምጣት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
ያለፉት ስድስት ወራት ከወትሮው በተለየ ዕቅዶቻችን ላይ የጋራ መግባባትና የይዘት ለውጦችን ወደ ስራ በማስገባት ጅምር መልካም አፈፃፀሞች መጥተዋል ብለዋል። ጥራት ፣ ይዘት ፣ ቀልጣፋና ፈጣን መረጃን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ክፍተቶችን የመሙላት ስራ ይሰራል ብለዋል ስራ አስኪያጁ። የህዝብ ቅሬታዎችን ፣ የሰላም ፣ የልማት ፣ የመልካም አስተዳደርና የመዝናኛ ስራዎችን ጨምሮ በሁሉም ተደራሽ ለመሆን ዝግጁ ነን ብለዋል።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ መድረኩን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ4 ጣቢያዎች በ12 ቋንቋዎች ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉ መንግስትና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ከጣቢያዎቹ ጋር ተቀራርቦ እየሰሩ መሆኒቸውን ጠቁመዋል።
የሚዛን ቅርንጫፍ መልካም እና በርካታ ተግባራት በጠንካራ ጎን የሚጠቀሱ አፈጻጸሞች እንዳሉ ጠቁመው ጥራት ፣ ፍጥነትና የሚዲያ አማራጮች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ተቋሙን በስራዎቹ ማስተዋወቅ ፣ የማርኬቲንግ ስራዎች ማስፋትና ከተቋማት ጋር መልካም ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ፣ የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትና የጣቢያው አመራሮች በመድረኩ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነዉ።
