የአንድነታችን አርማ የሆነውን የዓድዋ ድል በኢኮኖሚው መስክ ለመድገም እየሠራን ነው – የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች

Spread the love

የኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዓርማ የሆነውን የዓድዋ ድል በኢኮኖሚው መስክ ዳግም ለማስመዝገብ እየሠራን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

ድሉን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን አይሽሬ ጀግንነት ማሳያ ነው ብለዋል።

አቶ በለጠ ባሾ የዓድዋ ድል ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በአንድነት ያሸነፉበትና የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁበት አኩሪ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

ቅድመ አያቶቻችን ከአራቱም ማዕዘን ወደ ዓድዋ ተራሮች በመትመም ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ውድ ህይወታቸውን ሰጥተዋል ያሉት አቶ በለጠ፤ ድሉ የኅብረብሔራዊ አንድነታችን አርማ ነው ብለዋል።

አቶ ተሾመ በላይነህ እና ወጣት ኢዮብ አትርሳው፥ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የተባበረ የጀግንነት ክንድ ጠላትን አሳፍረው የመለሱበት ዘመን ተሻጋሪና አንጸባራቂ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት ጥንካሬ በዓለም የታየበት፣ ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ብርሃን የፈነጠቀ እና ለዛሬው ትውልድ ኩራትን ያስተላለፈ ድል መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌላኛው የታርጫ ከተማ ነዋሪ አቶ ጥላሁን ደምሴ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከቅድመ አያቶቻቸው በወረሱት ጀግንነት ሀገርን በማልማት ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ልክ እንደ ዓድዋ ድል በህብረ ብሔራዊ አንድነታችን በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ብሔራዊ የኩራት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ከተረጂነት ተላቃ ወደ ውጭ እስከ መላክ መድረሷን ገልጸው፤ ይህም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የጀመርነው ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቱሪዝም፣ በኮሪደር ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎችም መስኮች ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመጥቀስ ይህም ለትውልዱ በሁሉም መስክ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል በጀግኖች መስዋዕትነት የተገኘ ድል መሆኑን ያነሱት አስተተያየት ሰጪዎቹ፤ በዚህ ዘመን ያሉ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለተጨማሪ ድል መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

እነሱም በአካባቢያቸው በልዩ ልዩ የልማት ዘርፎች በንቃት በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ በማንሳት፥ ወጣቶች ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ተግተው መስራት እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *