የፓርቲው የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎችን ማጠናከር ይገባዋል

Spread the love

የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተልዕኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ድጋፉን እንዲያጠናከር የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አመለከተ።

የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በየደረጃው ከሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና ስነ ምግባር ኮሚሽን አባላትና አመራሮች ጋር በፀረ ሙስና ትግልና ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሂደት ላይ መክረዋል።

የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ኮሚሽኑ በተቋማት ግንባታና የሰው ሃይል ልማት እንዲሁም በቤተሰብና ትምህርት ቤት ደረጃ የትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታ ላይ እየሰራ ነው።

ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ በመንግስት ተቋማት ጠንካራ ስራ ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግና የተመዘበረውን ሀብት በማስመለስ ረገድ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተልዕኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የፓርቲው የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽኑ መደገፍና የተገኘውን ውጤት በኦዲት መለየት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስታ ተስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመዘንጋት ሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ እንዳይዘፈቁ የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽኑ ጠንካራ ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

ኮሚሽኑ እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅርና ግልጽ አሰራር በመዘርጋት የአባላትንና አመራሩን ግልጽ መመሪያ በማውጣት ወደ ተግባር ገብቶ ውጤት እያመጣ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም ከ15 ሚሊዮን በላይ አባላትና በየደረጃው ያለውን አመራር በስነ-ምግባር በመገንባት ብቁ መሪዎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ ከፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ጋር በየደረጃው የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።

በመድረኩ የፌዴራልና የክልሎች የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነሮችና ምክትሎቻቸው እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው የኢንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ጽሕፈት ቤቶች አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *