





አሰባሳቢ ትርክቶችን በማጎልበት በህዝቦች መካከል አብሮነትንና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው ”አብሮነት ስለ ኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት በሐረር ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የባህል፣ የስፖርትና ማህበራዊ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሙና በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነን ጨምሮ ምሁራን፣ የኪነጥበብና የስፖርት ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለፁት በህዝቦች መካከል አንድነትና አብሮነት እንዲጎለብት መንግስት መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ባህላዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት በማህበረሰቡ መካከል አንድነትና አብሮነትን ለማጎልበት በተከናወነው ስራ ውጤት እየታየ መምጣቱንና የወል ትርክትም እየተገነባ መሆኑንና ይሄም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩም ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱ ሃሳቦችን የእቅዱ አካል አድርጎ እንደሚሰራ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ የወል ትርክት የመገንባቱ ጉዳይ በተለይም በባህል፣ በስፖርትና በኪነ ጥበብ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው መድረኩ አሰባሳቢ የወል ትርክቶችን ለማጉላት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የጋራ የሆኑ የሚያስተሳስሩንና አንድ የሚያደርጉን እሴቶቻችንን በመጠቀም ሰላም፣ አንድነትንና አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከመድረኩ በተጓዳኝም የአገር አንድነትና አሳባሳቢ ትርክት የሚያመላክቱ ፎቶዎች በአውደ ርዕይ ለእይታ ቀርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
