በግንባታ ላይ የሚገኙ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀዉ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው፦ኢንጂነር በየነ በላቸው

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት 61 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ64ሺ በላይ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የክልሉ ውሃ፣ ማዕድና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው የተመራ ልዑክ በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ በግዝመሬት እና ሺሚ ቀበሌዎች በግንባታ ላይ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ምልከታ አድርጓል።

በጉብኝቱ የቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው እንደገለጹት እየተገነቡ የሚገኙ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀዉ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው ።

ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበት የተገነባዉ የመጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ በመስመር ፍተሻ ላይ እንደሚገኝ በመስክ ምልከታዉ ማረጋገጡንም የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ለ5400 ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እየተሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት እንደሆነም ጠቅሰው ይህም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።

ቢሮ ኃላፊዉ በግማሽ በጀት አመት 8 ፕሮጀክቶች በክልል መንግስት፣ 32 አነስተኛ ፕሮጀክቶች በዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም 21 ፕሮጀክት በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በድምሩ 61 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ64ሺ ህዝብ በላይ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አያይዘው ተናግረዋል።

በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ እየተሰራ እንደለም የጠቆሙት የቤንች ሸኮ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወልዲየስ ዘለቀ በዞኑ ውስጥ በክልልና በዞኑ መንግስት እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ህዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሸኮ ወረዳ የግዝመሬት እና ሺሚ ቀበሌዎች እየተገነባ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ባጠረ ጊዜ ውስጥ ቀሪ ስራዎችን አጠናቀዉ ለማስረከብ እየተሰራ መሆኑን መልካሙ ግዛው የውሃ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሥራአስኪያጅ ኢንጂነር መልካሙ ግዛው ጠቁመዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *