የዓድዋ ድል ዛሬም ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት በሚተጉ ልጆቿ ዳግም እየተገለጠ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

Spread the love

የዓድዋ ድል ዛሬም ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት በሚተጉ ልጆቿ ዳግም እየተገለጠ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ ለአፍሪካውያንና መላ ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነና የሴቶችን የፖለቲካ ጥበብ ያሳየ ነው።

የዓደዋ ድል ለአፍሪካውያንና ለመላ ጥቁር ህዝቦች ተስፋንና ድልን ያበሰረ ቅኝ ገዥዎች ሊያጠፉት የነበረን ሰብአዊ ክብር መልሶ ያጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ድሉ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጀግንነት ያሳየ በተለይም የሴቶችን ብርቱ ተሳትፎና የፖለቲካ ብልሀት የገለጠ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የዓድዋ ታሪካዊ ዳራ ትጉህ የዕውቀት ሃይልና የሀሳብ የበላይነት ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል ዛሬም ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት በሚተጉ ልጆቿ እየተገለጠ የሚገኝ ሃይል መሆኑን ጠቁመው፤ ነገም በልጆቿ ጸንቶ የሚቆይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ድሉ ኢትዮጵያውያን ከራስ አልፎ ለሌሎች የነበራቸውን ክብር ያሳዩበት መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ከዓድዋ በፊትም የነበረ አሁንም ያለ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ እንዲገለጥና እንዲበራ የዓድዋ ድል ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚተጉ ጀግኖች በየዘመኑ እየተፈጠሩ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ውጤታማ በማድረግ የኢትዮጵያን ታላቅነት ማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም ገልጸዋል።

ትውልዱ በጥበብ፣ በዕውቀትና በስራ በመትጋት የዓድዋን ገድል እንዲደግምም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል ሲል ኢዜአ ዘግቧል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *