የዓድዋ ድል አፍሪካ እጣ ፋንታዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ መበየን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው፦የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት

Spread the love

የዓድዋ ድል አፍሪካ እጣ ፋንታዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ መበየን እንደምትችል ያረጋገጠ ነው ሲሉ የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ገለጹ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

የቀድሞው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ጦርነትን የማሸነፍ ታሪክ ብቻ አደለም ብለዋል።

የዓድዋ ድል ለመላ ጥቁር ህዝቦች የይቻላል አስተሳሰብን ያሰረፀ እንዲሁም በአንድነትና ትብብር የአፍሪካን መፃኢ ዕድል የተሻለ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ ለደረሰባት በደል ካሳ የምትጠይቅበት ዓመት እንደመሆኑ በዓሉ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ነው ያሉት።

አፍሪካውያን ከተባበሩና በአንድነት ከቆሙ የማይሳኩ የሚመስሉ ድሎችን ማስመዝገብና የተሻለ አህጉር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲልና የአፍሪካውያን ተምሳሌት መሆኗንም በቅርቡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉ የልማት ስራዎች ምስክር ናቸው ብለዋል።

ድሉ አፍሪካ የራሷን እጣ ፋንታ ያለማንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት መበየንና መቅረፅ እንደምትችል ያረጋገጠ መሆኑንም በአፅንኦት ገልጸዋል።

የዚህ ዓመት የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ ለአፍሪካውያን እና ትውልደ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትህን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው የዓድዋ ድል ይህንን የካሳ ጥያቄ ያቀጣጠለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካውያንን ያላለቀ የቤት ሥራና የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ ለማሰጠትም በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን እንዲታገሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *