ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ጉቦ የተቀበለ አመራርን ለህግ ማቅረቡን የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

Spread the love

ህብረተሰቡ አገልግሎትን በምልጃና ጉቦ ለመፈፀም የሚፈልጉ አመራርና ሰራተኞች ላይ የተለመደውን ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር ዳግም ዳንኤል እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከህብረተሰቡ የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ የማጣራትና በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው የፍትህ አካላት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ዳግም እንደገለጹት በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ አቶ ገረመው አብርሀም በወረዳው የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው እየሰሩ በነበሩበት ወቅት የወረዳው ያወጣውን የመንገድ ስራ ጨረታ ተወዳድረውና አሸንፈው ወደ ስራ የገቡ ኮንትራክተሮች የሰሩበትን ክፍያ ትዕዛዝ ለመፈፀምም ሆነ ከተቋሙ አገልግሎት ፈልገው ከመጡ ተገልጋዮች ምልጃ ሲቀበሉ ነበረ ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ ያገኘውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ባደረገው ምርመራ ግለሰቡ የተሰጠውን የህዝብና የመንግስት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተለያዩ ጊዜያት ከላይ ከተጠቀሱት ግለሰቦች ከ490ሺ 534 ብር በላይ ጉቦ መቀበሉን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ጉዳዩን ለማየት በህግ ስልጣን ለተሰጠው የፍትህ አካል ቀርቦ አስፈላጊው ስራ እየተሰራ ሲሆን ግለሰቡም በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነር ዳግም አክለውም በቀጣይም ኮሚሽኑ ጉዳዩን ተከታትሎ የተሰጠውን ውሳኔ ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡም እንደዚህ አይነት ህዝብን የሚያማርሩ ፣ በጉቦና እጅ መንሻ የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡ አመርና ባለሙያዎች ላይ የተለመደውን ጥቆማ በመስጠት ኮሚሽኑ የጀመረውን የጸረ ሙስና ትግል እውን እንዲሆን የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *