




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አለም አቀፋ የአካል ጉዳተኞች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል።
በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ32ኛ በክልሉን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የርዕሰ መስተዳደሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ክብር አቶ ደነቀ ማሞ አካል ጉዳተኝነት አለመቻልና ብቃት ማጣት ሳይሆን ባላቸው ዕውቀትና ችሎታ ዜጋን የሚቀርጹ፣ ለሀገር ዕድገትና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ዜጎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኞች የሚያካትት ምቹ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳርን መፍጠር ከመንግሥት እና ከሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጠበቅበትም የጠቀሱት አቶ ደነቀ አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ ዕድገትና ልማት ላይ ጉልህ ሚና እንዲያበረክቱ የሁሉም ርብርብና ቅንጅታዊ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ም/ቢሮ ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ራሄል ሌዊ በበኩላቸው አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮ ወይም ሰዉ ሰራሽ በሆነ ሁኔታ በማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል ዉስጥ በማንኛዉም ቦታና ጊዜ የሚፈጠር ክስተት እንጂ የእርግማን ወይም የዓምላክ ቁጣ አይደለም አይደለም ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች ምቹ የስራ ሁኔታ ከተመቻቸላቸዉ መስራትና ለሀገር ብልፅግና የበኩላቸዉን አስተዋጽዎ ማበርከት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
አክለውም ዛሬ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች መብቶችና ደኅንነቶች የማስጠበቅ ፣ የማስፋፋትና የመወሰን ደረጃውን ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።
የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተረፈ ጌታቸው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰቡ ውስጥ እንደሚገኝና አንድ የመንግስት ተቋም ለአካል ጉዳተኝነት በሥርዓተ ትምህርት ተካትቶ ከሚሰጠው የትምህርት መስመር (የአካቶ ትምህርት) ባሻገር በአካባቢያችን ለሚገኙ ማናቸውም የአካል ጉዳተኞች አቅም በፈቀደ መጠን የትምህርትና የሥልጠና ዕድሎችን በማመቻቸት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አካል ጉዳተኞችን በትምህርት፣ በስራ እና በጤና ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን በመስራት ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ቀጣይ የፍትሃዊነት ጥያቄም የሚያስነሳ እንዳይሆን ያሉት የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አደም አሊ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰባቸውን የቤንች ሸኮ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመልክታል።
በበዓሉም ለክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት የገንዘብ ድጋፋ፣ለ6ቱም ዞኖች የዊልቸር ድጋፍ ፣የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት የመስጠት ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን የሚዛን አማን የአካል ጉዳተኞች የተሀድሶ ማዕከል ግንባታ ምልከታ ተደርጓል።
