



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ የጌጫ ከተማና ጋቲባ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ያነጋገርናቸው የጌጫ ከተማና ጋቲባ ቀበሌ ነዋሪዎች በወረዳው የንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በጌጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ የነዋሪዎች ረጅም ዓመታት ጥያቄ ከመሆኑም በላይ ንጽህና ያልጠቀውን ውሃ ከተለያዩ ምንጮች በመጠቀማቸው ራሳቸውንና የቤተሰብ አባሎቻቸው በተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታ ከመጠቃትም በላይ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት ለመስጠት ይቸገሩ እንደነበረ ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን የውሃ ተቋማት ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃታቸው ችግሩ በመቀረፉና አዲሱ ክልል በሰጠው ትኩረትና ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን የከተማ ነዋሪዎቹ አቶ እስራኤል እሸቱና ወ/ሮ አበባየሁ ዲኖ ተናግረዋል።
የጋቲባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታርኩ ሸነኖ እና ወ/ሮ ዘነበች ገቢቶ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ንጹህ የመጠጥ ውሃ በአካባቢው ባለመኖሩና ከሩቅ የወራጅ ወንዝ በመጠቀማቸው ውሃ ለማግኘት ብዙ ርቀት በመጓዝ መቸገራቸውን በማንሳት አሁን የማያቋረጥ የቦኖ ውሃ ከመጠቀምም አልፎ ቤት ለቤት ለማስገባት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የጋቲባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ከነዋሪዎች በተጨማሪ የመንግሥትና ሀይማኖት ተቋማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አሰተያየት ሰጪዎቹ አንስተዋል ።
የጌጫ ከተማ ውሃ ፕሮጀክት የለውጡ መንግስት ትሩፋት እና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ መሆኑን የጠቀሱት የአንድራቻ ወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የባህል ቱርዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መብራቴ ጌታሁን ናቸው።
ፕሮጀክቱ ከ94ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በክልሉ፣ በዞኑና ወረዳ መንግስት ማቺንግ ፈንድ ትብብር 13ሺ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተገነባ መሆኑን አቶ መብራቴ አንስተዋል ።
ከዚህ በፊት በወረዳው ከፍተኛ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርና ዝቅተኛ ሽፋን መኖሩን ያወሱት ምክትል አስተዳዳሪው የጌጫ ከተማ እና የቱጉሪ ጋቲባ የውሃ ፕሮጀክት በመጠናቀቁ ሽፋኑን ከማሳደግም በላይ ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑን ማሳያና የህብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳውም ሆነ በከተማ ከፍተኛ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መኖሩን በማንሳት ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ችግሩን ለመፍታት ብዙ የውሃ ተቋማት ግንባታ መጀመሩንና ከነዚህም የገጫና ጋቲባ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን የተናገሩት የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ብዙአየሁ ከፍታው ናቸው።
አቶ በላይ እንዳሻው የገጫ ከተማ ውሃ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ የፕሮጀክቱ ግንባታ 13 ኪ/ሜ ከዋናው ምንጭ የመስመር ዝርጋታ፣ 300ሜትርክ ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚችል ማጠራቀሚያ ታንከር፣ ሁለት ቦኖ እና የቢሮ ግንባታ ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል ።
የፕሮጀክቱ ጊዜያዊ ርክብክብ ከተደረገ በኃላ በውሃ አጠቃቀም፣ በቆጣሪ ቤት ለቤት ዝርጋታ ፣መስመሩ ባልተዳረሰባቸው የማስፋፊያ ስራ፣በወጭ መጋራት ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር በተሰራው ስራ 1000ሜ የመስመር ዝርጋታና 450 አዲስ ቆጣሪ ማስገባት መቻሉን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል ።
የጋቲባ ቀበሌ የውሃ ፕሮጀክት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በOne Wash ፕሮጀክት ድጋፍ ተገንብቶ የሁለት ቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን የወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ቆጭቶ ታፈሰ ገልጸዋል።
ውሃው ከቱጊሪ ቀበሌ በመነሳት እስከ ጋቲባ 3 ኪ/ሜ የመስመር ዝርጋታ የተደረገለትና በግንባታው ሂደት 100ሜትር ኪዩብ ዉሃ መያዝ የሚችል የማጠራቀሚያ ታንኬርና 7 ቦኖዎችን ያካተተ ነው ያሉት አቶ ቆጭቶ የውሃ መጠኑ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በጋቲባ ከተማ ቤት ለቤት ዝርጋታና በተጨማሪም 3ኛ የሼበና ቀበሌና በጋቲባ ቀበሌ ዝርጋታው ያልተዳረሰባቸውን አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል ።
የተገነባውን የውሃ ተቋማትን በዘላቂነት ለመጠቀምና አጠቃቀምን ፍትሐዊ ለማድረግ የመተዳደሪያ ደንብን በማዘጋጀት የውሃ ኮሚቴን በማቋቋም በአሰራር ዙሪያ ስልጠና በመስጠት እየተሰራ ከመሆኑም በላይ የተሰበሰበው ገንዘብ በኦሞ ባንክ ከየተጠራቀመ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
የውሃ ችግሩ በፊት ከነበረው በመፈታቱ መንግስትን ያመሰገኑት ነዋሪዎቹ በገጫ ከተማ የመብራት መቆራረጥ ችግር ለውሃ አገልግሎት ማነቆ መሆኑን እና በጋታባ ውሃ አቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም መስመርን በማስፋፋት ሁሉን ህብረተሰብ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ውስንነት መኖሩን አስተያየት ሰጪዎች አንስተው የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪውም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከተው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጌታሁን ግርማ
