


ባህል የአንድ ብሔረሰብ ማንነት መገለጫው፤ ትልቅ እሴቱ ነው። ባህልን ማልማት፣ ማሳደግ ለትውልድ ማሸጋገር ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ አደራው ነው። ይህ ትልቅ አደራ ሳይሸረፍ፣ሳይበረዝ የጥንት ይዘቱን ጠብቆ እንዲለማ ማድረግም ያስፈልጋል።
በክልላችን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ የፃራ ብሔረሰብ ነው ። ብሔረሰቡ የራሱ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች አሉት ።ከእነዚህ እሴቶች ውስጥ አንዱ ባህላዊ አለባበስና አጋጌጥ ተጠቃሽ ነው ።
በፃራ ብሔረሰብ ሴቶች ከሚያዘወትሩት የአለባበስ አይነቶች ውስጥ ደግሞ ካንካርና ኩችጓ ተጠቃሽ ናቸው።
ካንካር በሴቷ ክርን ላይ ከአልሙኒየም ብረትወይም ኮዳ ከሆነ ብረት ተቀጥቅጦ የሚሰራና ለውበት በላይኛው ክንድ ላይ ተደርጎ ለውበት የሚጠቀሙበት አጋጌጥ ነው። ኩችጓ ደግሞ ከጥይት ቀለሃ ተቀጥቅጦ የሚሰራ የእጅ አምባር ነው ።ይህም አንዱ የብሔረሰቡ ማጌጫ ቱባ ባህሉ ነው።
የፃራ ብሔረሰብ ሴቶች በዚህ ብቻ አይወሰኑም ከጨሌና ከእንጨት ቅርፊት ተሰርተው በአልባሳትነት የሚገለገሉባቸው አለባበሶች ስለመኖራቸው በካፋ ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ አባል ሆና እየሰራች ያለችሁ ወጣት አልማዝ ቡሾ ታስረዳለች።
ወጣት አልማዝ እነዚህንና ሌሎችየብሔረሰቡ መገለጫዎችን አልባሳት በመልበስና በማሸብረቅ ዛሬ ላይ በአደባባይ በዓል ለዓለም ባህላዊ አለባበሷን አሳይታለች ። ወጣት አልማዝ ከላይ የገለጽናቸውን አለባበሶች እሷም ተላብሳ ሌሎችም እንዲላበሱ ጥሪ አድርጋለች። በራስ ቅል የሚታሰር ጨሌ ለደስታ ጊዜ በተለይም በሰርግ ወቅት እንደሚጠቀሙትም ተናግራለች ። በአንገት ላይ ያሉ በርካታ የጨሌ አይነቶችም እንዲሁ ለደስታ ጊዜ የሚለበሱ ስለመሆኑም አብራርታለች። በወገብ ላይ የሚታሰር ጨሌ ከተለያዩ ቀለማት የሚዘጋጅና የራሱ የሆነ ትርጉም እንዳለው ወጣት አልማዝ ነግራናለች።
ወጣት አልማዝ ጥንት የብሔረሰቡ ተወላጆች ዘመናዊ ልብስ ከመምጣቱ በፊት ከእንጨት ቅርፊት የሚሰራ ጉርድ አልባሳትን ይጠቀሙ እንደነበርና ይህንን ጥንታዊና ታሪካዊ አለባበስ ዛሬ ለዓለም አሳይታለች።
የአሁኑ ትውልድ ይህንን ትልቅ የትውልድ ቅብብሎሽ አደራውን በተገቢው እንዲወጣና ይበልጥ ተጠናክሮ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲተላለፍ በተተኪው ትውልድ ላይ መንግስት ፣ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አድርገው ሊሰሩበት ይገባል ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
በታጠቅ አበበ
