



የውስጥ ጥንካሬ እና ዐቅም ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት ፋይዳዉ የላቀ በመሆኑ በዚህ ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡
“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት ለኮሙኒኬሽን ዘርፉ የክልል እና ከተማ አስተዳደር መዋቅር አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዲስአበባ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና በሁለተኛ ቀን ውሎዉ ጂኦ-ፖለቲካዊ ዓውዶች እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አተኩሮ ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናዉን የሰጡት የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገር እና ጠጣር ውስጣዊ ዐቅሞችን ማጎልበት ለውጭ ግንኙነት ስኬታማነት የላቀ ሚና ያላቸው መኾኑን በማስገንዘብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ እነዚህን ዐቅሞች ለማጎልበት የተቀረጹ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ማስገንዘብና ማስረጽ ላይ እንዲያተኩር አሳስበዋል፡፡
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን፣ የመንግሥት መነሣሣቶችን በአግባቡ ማስገንዘብ፣ ቀጣናዊ እና ዓለማቀፋዊ አዝማሚያዎችንና አንድምታቸውን የተመለከቱ ወቅታዊ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን መስጠት ለሀገራዊ ገጽታ መገንባት እና ለዲፕሎማሲ ስኬት ፋይዳቸዉ ጉልህ መሆኑን አቶ ተስፋሁን አብራርተዋል፡፡
በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የተቀናጁ፣ የተደራጁ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት ዜጎች የሀገራቸዉን መሻት እና ዕቅድ ተገንዝበዉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ዲፕሎማት እንዲኾኑ ማስቻል ይገባል ብለዋል፡፡
ዐዲሱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እሳቤ ወቅታዊ ነባራዊ ዓውዱን ያገናዘበ፣ ለኢትዮጵያ ሕልሞች መሳካት ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ እና ቅድሚያ ለጎረቤት የሰጠ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ዜጋ ተኮር የሚለው አዲሱ እይታ በተለያዩ ሀገራት በሰቆቃ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አውስተዋል።
የሥልጠናዉ ተሳፊዎች በበኩላቸው ለዘርፉ በተከታታይ እየተሰጡ ያሉ የፖሊሲ እና የዐቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ጥልቀት ያለዉን ግንዛቤ እየፈጠሩ፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሳካት እያስቻሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
