ሪፖርታዥ

Spread the love


የክልላችን የበልግ ስራ እንቅስቃሴ

በሀገራችን ታርክ የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ለረጅም ዓመታት ብቻውን የመሪነት ሚና ሲጫወት መቆየቱና አሁንም ትኩረት ከተሰጣቸው የብዝሀ ኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብዙ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነው። ከነዚህም አንዱና ጉልህ ሚና ያለው የክልሉ ግብርና እና የተፈጥሮ ዘርፍ ነው።

የክልል ግብርና ቢሮው የተፈጥሮ ሀብት እንዳይጎዳ በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በማልማት በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ፣ የስራ ዕድልን በመፍጠር፣ የውጭ ኤክስፖርት ምርቶችን በመጨመር የውጭ ምንዛሪን በማሳደግ፣ ከውጭ የሚመጡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ።

ቢሮው የተቋሙ ተልዕኮን ለመወጣት የግብርና ተግባራትን በተለያዩ የአዝመራ ወቅት በማከፋፈል አቅዶ የተለያዩ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና በማቀናጀት፣ አስፈላጊ ግብዓትና ቴክኖሎጅን በማሟላት ስሰራ ከመቆየቱም በላይ በዘርፉ አመርቂ ውጤትም በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።

በመሆኑም በዛሬው ዝግጅታችን የክልሉ ግብርና ቢሮ የበልግ ስራዎች እንቅስቃን እንመለከታለን።

ቢሮው በ2017 ዓ/ም በበልግ ወቅት በአዝርእት ሰብሎች 359,375ሄ/ር እና ማሳ በማልማት 12.3 ሚለየን ኩ/ል ምርት ለማግኘት፣ በሆርቲካልቸር ዘርፍ 75,629ሄ/ር በላይ ለማልማት ታቅደው እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ገልጸዋል ።

የአዝመራ ወቅቱን ዕቅድ ለማሳካት የዝግጅት ምዕራፍ ስራውን ስኬታማ በማድረግ ፈጻሚን ከማዘጋጀት በክልል ደረጃ ከ250 ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት በክልሉ የንቅናቄ መድረክ ማሳተፍ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በ40 ወረዳና በ20 ከተማ አስተዳደር የንቅናቄው መድረክ ከመካሄዱም በላይ ዘርፉ በመፋዘዙ ምክንያት ችግሩን ለመፍታትና ለማነቃቃት 3600 የሚሆኑ የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች በግምገማ የማጥራት ሂደት በማለፋቸው የራሳቸውን ዕቅድ በማቀድ በግቡ ላይ ተፈራርመው ወደ ስራ መገባታቸው ለበልግ ስራ ከወትሮ የበለጠ መነቃቃት መፍጠሩን አቶ አሸናፊ አንስተዋል።

በክልሉ ያለውን አቅም ታሳቢ ያደረገ ዕቅደ መታቀዱን ያነሱት የቢሮ ም/ኃላፊ ምርትና ምርታማነት ሊያሳደጉ የሚችሉ የተለያዩ የምርታማነት ማሳደጊያ ፓኬጆችና ተግባራት የዕቅደ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የግብዓት አጠቃቀምና ስርጭትን በሚመለከት ከ156ሺ የአፈር ማዳበሪያ በስድስት ዞኖች ተሰራጭተው ወደ አርሶ አደር በማድረስ ላይ ነው ብለዋል።

የምርጥ ዘር ስርጭትን በሚመለከት እጥረት ያለመኖሩን ጠቅሰው ከታቀደው 21,578ኩ/ል ውስጥ 50% ያህሉ ወደ ክልል የገባ ሲሆን 8000 ኩ/ል ወደ አ/አደር መሰራጨቱን ጨምሮ አብራርተዋል ።

የአፈር ማደበሪያ ቴክኖሎጂን ከመጠቀምም ባሻገር የኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት፣ መካናይዜሽን እርሻ ማሳረስ፣ የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ማከም የምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጆችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በበልግ አዝመራ ወቅት 106,000ሄ/ር በኩታ ገጠም እርሻ በማልማት እየተሰራ ያለ መሆኑን በመጥቀስ ይህም ምርታማነትን ለመጨመር ጉልህ ሚና መኖሩን አንስተዋል ።

የአፈር ለምነትን ለማሻሻል 26,200ኩ/ል ኖራ መሠራጨትን፣ በመካናይዘሽን ከ30,000ሄ/ር በላይ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል ።

በተጨማሪ የጥራጥሬ ምርታማነት ማሳደጊያ 12,300 በላይ ሳቼት ህያው ማዳበሪያ ማቅረብ መቻሉን፣ ለአትክልት ልማት ከ36ሺ ቶን በላይ ኮምፖስት በአርሶ አደሩ ዘንድ እንዲዘጋጅ ተደርጎ በጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ አጠቃላይ ዕቅድ 93.2% ወይም 335,000ሄ/ር ማሳ መታረሱን የገለጹት አቶ አሽናፊ 131,000ሄ/ር መዘራቱንና ከተዘራው ውስጥ 20,000ሄ/ር ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሙሉና በተሟላ ፓኬጅ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል ።

በዚህ ሂደት እስካሁን ከ17,000ኩ/ል በላይ NPS፣ 4,000ኩ/ል ዩሪያ እና ከ2500ኩ/ል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል ።

በክልሉ በበልግ ወቅት የሚለሙ ዋና ዋና አዝርዕት ሰብሎችን በሚመለከት ከ70% በላይ(245,000ሄ/ር) ማሳ በበቆሎ የሚሸፈን ሲሆን በልዩ ትኩረት እየለማ ያለው ሩዝ 24,000ሄ/ር፣ቦሎቄ 50,000ሄ/ር እና ማሽላ 16,000 ሄ/ር እንዲሁም ሌሎች በመሸፈን ምርትን ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በሆርቲካልቸር ሰብሎች 75,629ሄ/ር ማሳ በማልማት 17.2 ሚሊየን ኩ/ል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያስታወሱት የቢሮ ም/ኃላፊው 41% የማሳ ዝግጅት መደረጉንና ከተዘጋጀው ማሳ 60% በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል ።

በሆርቲካልቸር ሰብሎች ሁሉም ከፍተኛ ድርሻ መኖራቸውን ያነሱት አቶ አሸናፊ በበልግ ከሚለማው በተጨማሪ እንሰትን በልዩነት እየተሰራ በመሆኑ ወደ 81ሚለየን ችግኝ በማዘጋጀት ከ30,000ሄ/ር በላይ በንቅናቄ መትከል መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል ።

የታቀደውን ዕቅድ በማሳካት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በክልሉ የምግብ ሉአላዊነት ከማረጋገጥ በሚሰራው ስራ በተቀናጀና ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልክ ከክልል እስከ ወረዳ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በበልግ እርሻ ወቅት ወደ ቤንች ሸኮ ዞን የገባው የዲኬ በቆሎ ዝሪያ ብልሽት በመኖሩ ቶሎ ያለመብቀል፣የበልግ ዝናብ ዘግይቶ መግባት፣ እንደየአካባቢው የዝናብ መብዛትም ሆነ ማነስ እያጋጠመ መሆኑን እንደ ማነቆ አንስተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ዲኬ ዝሪያ እንዳይዘራ፣ በዝናብ መዘገየት ምክንያት ቀድሞ የተዘራ በቆሎ በጠፋበት ደጋና ወይናደጋ አካባቢ በማካከሻ ድንችና የመሳሰሉትን በመተካት ማሳውን በመሸፈን ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል ።

በመጨረሻም የዝናብ ስርጭቱ በአንዳንድ ቦታ የመብዛት በተቃራኒው የማነስ/ማጠር ሁኔታዎች እየተስተዋሉ በመሆኑ የወረዳ መዋቅር ግብዓት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የተሸከርካሪ ድጋፍ በማድግ ለአ/አደር በጊዜ ማድረስ እንዲሁም የልማት ጣቢያ ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ የዘር ሳምንትን በማወጅ በአጭር ጊዜ በቅንጅት ማሳውን በዘር መሸፈን ዕቅዱን ማሳካት እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *