



ሀገራዊ ልማት እና ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ የሚቻለዉ ቀጣይነት ያለው የምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ በመሆኑ ሀገራዊ ትልሞችን እና የመዳረሻ ግቦችን ማስገንዘብ ላይ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ እንዲያተኩር የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ መልእክት ለክልል እና ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዲስአበባ እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ዶ/ር ኢዮብ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሠረተ ሐሳቦችንና የተመዘገቡ ስኬቶችን አብራርተዋል፡፡
በማብራሪያቸዉም የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ “የሀገር ልማት የሁሉንም ርብርብ ስለሚጠይቅ ምልዓተ ሕዝቡን አስገንዝቦ ለላቀ ተሳትፎ እና ስኬት ማነሣሣት ላይ አተኩሮ መሥራት አለበት” ብለዋል፡፡ ይዘቶቹ የኢትዮጵያን ተስፋዎች፣ የዕድገት መሠረቶች፣ የልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ፋይዳ፣ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ ማመላከት ላይ አተኩረዉ መዘጋጀት እንዳለባቸዉም አመላክተዋል፡፡
የመጀመሪያዉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ ድርቅ እና ጦርነት የተፈተነ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ኢዮብ “በበርካታ ችግሮችም ውስጥ በአመራሩ ጥበብ የተሞላበት መሪነት ስኬት ያስመዘገበ ነበር” ብለዋል፡፡ በበርካታ ፈተናዎችም ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡን፣ ኢኮኖሚዉ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ዲጂታላይዜሽን መሸጋገሩን፣ አጠቃላይ ሀገራዊ ዕዳን ከነበረበት ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) የነበረውን ምጣኔ በመጀመሪያዉ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ወቅት በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን በማሳያነት አንሥተዋል፡፡
የአጠቃላይ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዉ የተረጋጋ ማክሮ-ኢኮኖሚ መፍጠርን፣ ዘላቂነትና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብን፣ የወጪ እና ገቢ ንግድን ማመጣጠንን፣ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ገብይት ሥርዐት መፍጠርን፣ የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት ማሻሻልንና የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኀዝ ማውረድን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ሚኒስትር ዴኤታዉ አስገንዝበዋል፡፡
ከተያዘዉ በጀት ዓመት መግቢያ ጀምሮ ወደ ተሟላ የትግበራ ምዕራፍ የገባዉ ሁለተኛዉ ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ስኬቶች እንደተመዘገቡበትም ዶ/ር ኢዮብ በገለጻቸዉ አመላክተዋል፡፡
ለአብነትም ባለፉት ዘጠን ወራት ብቻ 5.3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከወጪ ንግድ መገኘቱንና ካለፈዉ በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም አንጻር የ150% ዕድገት የታየበት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ አጠቃላይ የመንግሥት ገቢም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከባለፈዉ በጀት ዓመት አንጻር የ135% ዕድገት አስመዝግቦ ከ926 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ዶ/ር ኢዮብ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለተኛዉ ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተረጋጋ ማክሮ-ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ ምቹ የኢንቨስትመንት እና የገበያ ሥርዐት ለመፍጠር፣ የዘርፎችን ምርታማነትና ውጤታማነት ለማሳደግ እና ብቃት ያለው እና ውጤታማ የሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት እየሠራች ትገኛለች፡፡
ከመጋቢት 29/2017 ዓ/ም ጀምሮ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በየደረጃው ላሉ የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመለክታል ።
