መንግስት በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Spread the love

የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከ’ African Brains’ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮችና ልዑካን ቡድን አባላት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር ኢንቨስተሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት በጣም መሳኝ በመሆናቸው በዚህ ጉባኤ ትርጉም ያለውና የሚተገበር ውይይት እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በትምህርት ቤት ግንባታና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በድጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

እንደ አፍሪካ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው አሁን ያለንበት የአለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።

በመሆኑም ይህ በሦስት ቀን በትምህርት፣በቴኖሎጂና በክህሎት ዘርፍ የምናደርገው ውይይት በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በጉባዔውም ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ከክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *