



የዲሪ ማሻ አስፋልት መንገድ ግንባታ ዳግም መጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
የፌደራልና የክልል አመራሮች በተገኙበት ተቋረጦ የነበረው የዲሪ ማሻ አስፋልት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራ ትናንት ተጀምሯል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2010 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በሥራ ተቋራጭ አቅም ማነስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የዲሪ ማሻ አስፋልት መንገድ ዳግም ሥራ መጀመሩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚፈታ ታምኖበታል።
ከሰባት ዓመታት በኋላ በመንገዱ ዳግም መጀመርን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የመንገዱ አለመገንባት ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲዳርጋቸው ቆይቷል።
አሁን ላይ ግንባታው ሲጠናቀቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሰለሞን ገብረሚካኤል በአካባቢያቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ምርታቸውን ለገበያ ለማውጣት እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ አሁን ግንባታው በድጋሚ የተጀመረው ግንባታ ሲጠናቀቅ ይህን ችግራቸውን እንሚፈታላቸው ተናግረዋል።
ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመኖሩ ነፍሰ ጡር እናቶችንና ህሙማን ህክምና ለማግኘት በሚያደርጉት ጉዞ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ አቶ መንግስቱ ገዛኸኝ ናቸው።
የመንገድ አለመኖር የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የሰብል ምርቶችና እንስሳትን ለገበያ ለማቅረብ አዳጋች በመሆኑ በአካባቢያቸው ባሉ ገበያዎች በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው፣ የመንገድ ግንባታው ችግራቸውን አንደሚፈታ ተናግረዋል።
የገዋታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ሀይሌ የዲሪ -ማሻ አስፋልት መንገድ ግንባታ መጀመር የህብረተሰቡን የበርካታ ዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደሚመልስ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም መንገዱ ተጀምሮ መቆሙ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅ ግንባታው ዳግም መጀመር የወረዳውን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴን እንደሚያነቃቃውም አስረድተዋል።
ዞኑ በእርሻ፣ በእንስሳት እርባታ እና በማዕድን ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የመንገዱ መገንባት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ናቸው።
የዲሪ-ማሻ አስፋልት መንገድ የዞኑን አምስት ወረዳዎች ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ያለን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
የዲሪ-ማሻ አስፋልት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 61 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
የመንገዱ የምዕራፍ አንድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) እና ሌሎች የፌደራል፣ የክልልና የዞን የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ትናንት መከናወኑ ኢዜአ ዘግቧል።
