






በውድድርና ኤግዚቢሽን መድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደገለጹት፤ በፊት ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጠዉ ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በዘርፉ ውጤት ተገቢዉ ዉጤት ሳይመዘገብ ቆይቷል ብለዋል።
ለዚህም የተጀመሩ የተቋማት ግንባታዎች ተጠናቅቀዉ አገልግሎት ባለመስጠታቸውና ተቋማት በሚፈልገው ልክ ቴክኖሎጂ ከማሸጋገር አንጻር የነበራቸው ውስንነቶች ተግዳሮት እንደነበርም አስታውሰዋል።
ዋና አፈ-ጉባኤው የሥራና ክህሎት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ ምሁራኖች የሚፈልቁበትና ለቴክኖሎጅ ሽግግር ያለው አበርክቶ የላቀ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ልመራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስት ለበርካታ ጊዜያት ግንባታቸዉ ተጀምሮ የቆሙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ጊዜው የውድድርና የምርምር ጊዜ በመሆኑ በክልላችን በቴክኖሎጂና ምርምር ዘርፍ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅም ዋና አፈ-ጉባኤው አጥንኦት ሰጥቷል ።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አብይ አንደሞ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት በስነምግባር የተነፀና የፈጠራ ክህሎት ያለው የሰዉ ኃይል በመፍጠርና ድህነትና ኃላቀርነት ታርክ በማድረግ ረገድ እየተወጣ ያለዉን ሚና ማጠናጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።
በአዱሱ የለውጥ ዘመኑ የሚጠይቀዉን ፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎትና ምርምር ብቃትን በማዳበር በክልሉ ያለውን ፀጋ ማዕከል ያደረገ ጥራት ያለዉ ስልጠና በመስጠትና በቴክኖሎጅና በምርምር የማህበረሰቡ ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከርም አንስተዋል።
በክልሉ የክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ ሥልጠናና ምርምሮችን በማካሄድ አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ነዉ ዶክተር አብይ አንደሞ የጠቆሙት።
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምረት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸው ጊዜው የውድድርና የምርምር በመሆኑ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በተገቢው ልወጡ ይገባሉ ብለዋል።
በክልሉ ”ብሩህ አዕምሮዎች፤በክህሎት የበቁ ዜጎች በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የክህሎት፤ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርና ኤግዚቢሽን በሀገራችን ለ4ኛ ጊዜ በክልላችን ለ2ኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ሥራና ክህሎት ምክትል ኃላፊና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤቴልሔም ዳንኤል ናቸዉ።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በፈጠራ፣ክህሎትና በቴክኖሎጅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ በማፍራት ድህነትና በማስወገድ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከማበርከት ረገድ ያለዉ ሚና የጎላ በመሆኑ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ነዉ ያሉት።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጥራት ያለው ስልጠናና ምርምር ሥራዎችን በማካሄድ እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ላይ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በፍቅር ከበደ
