







የመንገድ ፕሮጀክቱ 64.8 ኪሎሜትር ርዝመት እንዳለውም ተገልጿል ።
የታርጫ ጪዳ መንገድ ተጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል።
ይህንን ፕሮጀክት ዳግም መጀመሩን በማስመልከትም ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የመንገድ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ መቋረጡ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን በእጅጉ የጎዳ መሆኑን አስታውሰዋል።
የብልጽግና ፓርቲ እና መንግስት ይህንን የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የሰነበተው የታርጫ ጪዳ አስፓልት መንገድ መልሶ ወደ ስራ ማስገባቱ የህዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ መገንባት ለዳውሮና ኮንታ ዞኖች ብቻ ሳይሆን ከአጎራባች ጅማና ወላይታ ዞኖች ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር በእጅጉ ያመልጣል ሲሉም ተናግረዋል ።
በዳውሮና ኮንታ ዞኖች ተጀምረው ያልተቋጩ የቦንጋ ፈለገህይወት አመያና የየዋካ ኢሰራ አስፓልት መንገድ የዕቀድ አካል ሆኖ ትኩረት እንዲሰጠውም የፌደራል መንግስትን ጠይቀዋል።
የኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ መጀመር ለአካባቢው የብልጽግና ጉዞና ለቱሪዝም መነቃቃት ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
የታርጫ ጪዳ አስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በተቋራጭ የአቅም ውስንነት መቋረጡንና ያለውን ችግሮች በመቅረፍ ዳግም ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓልም ብለዋል።
የመንገዱ መገንባት ለገበያ ልውውጥ፣ለቱሪዝም ዕድገት፣ለክልሉ ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለአካባቢው ነዋሪዎች አዳዲስ ዕድሎችን የሚፈነድቅ ነውም ብለዋል።
ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የአካባቢው አስተዳደር እና የህብረተሰቡ ትብብርና ድጋፍ እንዳይለይም ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር አለማየሁ አየለ በበኩላቸውም ለመንገድ ፕሮጀክቱ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ከፌደራል መንግስት መመደቡን ተናግረዋል ።
64.8 ኪሎሜትር የሚረዝመው ይኸው መንገድ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት በመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ተቋራጭና በዩኒኮን አማካሪ እንደሚሰራም አመላክተዋል ።
የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ በ2 ዓመት ከ6 ወራት ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅም የመሳይ ጠቅላላ ስራ ተቋሯጭ አስታውቋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ባስተላለፉት መልዕክትም የመንገዱ መገንባት በህብረሰቦች መካከል ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች በእጅጉ የሚያሳልጥ ነው ብለዋል ።
የኮንታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ወንድማገኝ ወጁ በበኩላቸውም መንገዱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ የመልሶ ማስጀመር ስነስርዓት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣የኢፌዴሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር አለማየሁ አየለ፣ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ እና የክልል እና የዳውሮ ዞን አመራሮችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በታጠቅ አበበ
