በክልሉ የማይነጥፍና ፍትሃዊ የንብረት ግብር ለመሰብሰብ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ግመታና አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፦ ወ/ሮ ሄለን ደበበ

Spread the love

የኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 ላይ የስልጠና መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡

የስልጠና መድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ የኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ ወ/ሮ ሄለን ደበበ በሪል ፕሮፐርቲ ግመታና ግብይት ወጥነት ያለው ስርዓት ለመዘርጋት እና የከተሞችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚፈለገውን መሠረታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በዘርፉ ለሚሰሩ ስራዎች ዕድገትና ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

የአሰራር ስርዓት በህግ ማዕቀፍ ለመደገፍ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጸድቆ ወደ ተግባር ምዕራፍ እየተሸጋገረ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከተሞች ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የንብረት ግመታና ገቢ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት ፍትሃዊና ግልጸኝነት የሰፈነበት ገቢ በመሰብሰብ ለከተማ ኢንቨስትመንት አመቺ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል፡፡

ታዓማንነት ያለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ስርዓት መዘርጋት የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረግ ግብይት ግልጸኝነት የሰፈነበትና በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ ለመወሰን አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የማይነጥፍና ፍትሃዊ የንብረት ግብርና ተያያዥ ገቢ የሚሰበሰብበት ስርዓት በሪል ንብረት ግመታና አሰራር ተግባራዊ በማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ከተሞቻችን የህዝብ ቁጥር እየጨመረና ከተሞች እየሰፉ መሆኑን ጠቁመው ተመጣጣኝ የሆነ የከተሞች መሠረተ ልማት ለማስፋፋት የሪል እስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በከተሞች መሠረተ ልማት ማሟላት እና ለህዝብ አገልግሎት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ኢንጂነር የማታለም ለዚህም ሀብት መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቦንጋ ከተማ ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣች ንግግር የለውጡ መንግሥት በተሰጠው ትኩረት ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለከተማ ነዋሪዎች አስፈላጊ አገልግሎት ለማሟላት በቂ የሆነ ሀብት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አስማማው ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው መሰብሰብ ያለበትን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ስራ ላይ ለማዋል ትኩረት የሚፈልግና ለዚህም የከተማ ገቢ አቅምን ለማሳደግ ከተለመደው አሰራር በመውጣት የአሰራር ስርዓቱን ማዘመን አስፈላጊ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ የፌዴራል ከተማና መሠረተ ልማት የዘርፉ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የክልሉ ከተማ ልማትና ክንስትራክሽን ቢሮ የየዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የሚዛን አማንና የቦንጋ ከተሞች የገቢና ማዘጋጀ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *