የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላምን ማፅናት ይገባል – ሰላም ሚኒስቴር

Spread the love

የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከርና ሰላምን ማፅናት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በፌዴራሊዝም እና በሰላም ማፅናት ጉዳዮች ላይ ለድሬዳዋና ሐረሪ ክልል የፍትህና የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች በድሬዳዋ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል።

የሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና የመንግስታት ግንኙነት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ቸሩ በወቅቱ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት ሰላምን በማፅናት የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በድሬዳዋ የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠናም በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የወል ትርክትን ለመገንባት ያለመ መሆኑን ጠቅስዋል።

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሰላም አህመድ በበኩላቸው፣ ስልጠናው ሰላምና አብሮነትን በማጽናት የፌዴራሊዝምና የብልፅግና ጉዞን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጎራባች ክልሎች የፍትህና ፀጥታ ተቋማት በቅንጅት የተጀመሩ የሰላምና መሰል ስራዎች እንዲጠናከሩ ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል።

ስልጠናው ሰላምና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በወል ትርክት ለማጀብ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ጠቁመው፣ ድሬዳዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአብሮነት ተፈቃቅረው የሚኖሩባት መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰላም ግንባታ ፋይዳ ያለውን ይህን የአብሮነት ባህል አጠናክሮ ለህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ግንባታ ለማዋል ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ብለዋል።

በምስራቅ ተጎራባች ክልሎች ያለውን ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ህብረ ብሔራዊነት ላይ መስራት የግድ ነው ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነስሪ ዘከሪያ ናቸው።

በስልጠናው የተሳተፉት የድሬዳዋ እና የሐረሪ ክልል የፍትህና ፀጥታ ተቋማት አመራሮች በበኩላቸው አብሮነትና ሰላምን ለማጽናት ቅንጅታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *