ቆይታ ከእኛ ጋር !

Spread the love

ባለፉት 9 ወራት በአንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት መርህን በመከተል ታቅደው በተከናወኑ ክልላዊ ተግባራት ዙሪያ ከክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ጋር ቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ፡፡


መ/ኮ፡-ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በቅድሚያ አመሰግናለሁ
እኔም አመሰግናለሁ ፡፡
መ/ኮ፡-ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልኝ ?
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡- ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል እባላለሁ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ
መ/ኮ፡-ባለፉት 9 ወራት የክልሉን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ እንዲያስችል ሀገራዊ አንድ ዕቅድና ሪፖርት መርህን ተከትሎ እንደ ክልል እየተሰራ ያለውን ስራ ቢገልጹልኝ ?
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡-  ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት መሰረቱ ከፌደራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው ዕቅድና ሪፖርት ተናባቢና ገላጭ እንዲሆን ታስቦ የመጣ ነው ፡፡በዚህም መሰረት ሁሉም ቢሮዎች ወይም ተቋማት የሚሰሩዋቸው ስራዎች በፌደራል ፕላንና ልማት ሚኒስቴር በቁልፍ አመላካቾች እንዲመዘኑ ለማድረግ ቁልፍ አመላካቾች ተለይተው የመጡበት ሂደት ነው ያለው ፡፡ እኛም እንደ ክልል ይህንን ወስደን የ10 ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ማዘጋጀት ችለናል ፡፡ ከዚህ አንጻር በየዓመቱ የሚሰሩ ስራዎች ከ10 ዓመቱ ተቀድተው የ2017 ዓ/ም የዕቅድ አካል ሆኖ ወደ ስራ ተገብቷል ፡፡ ይህንን በተመለከተም በስራ አመልካቾች መሰረት ምን ያህል ተሰራ የሚለውን በመከታተልና በመመዘን የተቋማትን ሪፖርት በመገምገም ተቋማት ያሉበትን ደረጃ የመለየትና የመደገፍ ስራዎችን አከናውነናል ፡፡ በአንድ ዕቅድ እና በአንድ ሪፖርት መርህ መሰረት በሰራነው ስራ በተቋማት ምን ያህል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ለማወቅ ችለናል  ፡፡
መ/ኮ፡- ይህንን ተከትሎም ባለፉት 9 ወራት በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ክልላዊ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዴት ይገለጻል?
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡-  ከካፒታል ፕሮጀክቶች አንጻር እንደ ክልል በርከት ያሉ ካፒታል ፕሮጀክቶች አሉ ፡፡አብዛኛዎቹ ነባር ፕሮጀክቶች  ናቸው ፡፡ ከክልሉ ምስረታ በፊት በቀድሞው ደቡብ ክልል ተጀምረው የነበሩ እና ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ይዘን መጥተናል ፡፡የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ አዳዲስ የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች አሉ ፡፡ከአፈጻጸማቸው አንጻር ባለን በጀት መጠን ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ተሞክሯል ፡፡በዚህ 9 ወራት መንግስት መድረስ በማይችልባቸው ማህበረሱቡን በማስተባበር እንደ መንገድና ድልድይ ተሰርተው እንዲጠናቀቁና ለአገልግሎት እንዲበቁ የተደረገበት ሂደት ነው ለው ፡፡ለአብነትም የያዶታ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ፣የቱም ንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ለአገልግሎት በቅቷል ፡፡ደቼ ደነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ፡፡ከትምህርትም አንጻር ትምህርት ለትውልድ በሚለው መርሃ ግብር ከ423 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ በርከት ያሉ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ስራ ተሰራበት ሁኔታ አለ ፡፡ ከጤና አንጻርም በሳይለም ወረዳ የያዶታ መለስተኛ ቀዶ ጥገና ማዕከል ፣በርከት ያሉ ጤና ኬላዎች ተሰርተው ለአገልግሎት ብቁ ሆነዋል ፡፤ እነዚህና ሌሎች በርከት ያሉ ፕሮጀክቶችን አስመርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ፡፡ በግንባታ ላይ ያሉ ሊጠናቀቁ የደረሱ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ ፡፡ ስለዚህ ባለን የበጀት መጠን እያየን እየሰራን እኛም በቅርበት ድጋፍ እና ክትትል እያደረግን ፕሮጀክት ስራዎች እየሄደ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ማለት ነው ፡፡
መ/ኮ፡-የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና መልክዓ ምድራዊ መረጃዎችን ከማሰባሰብና፣ከማደራጀትና ከመተንተን አኳያ የተሰራ ስራ ካለ ቢያብራሩ ?
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡-   በዚህ 9 ወራት ውስጥ ከተሰሩ ስራዎች አንጻር እንደ ቢሮ የሶሽዮ ኢኮኖሚክ መረጃዎችን፣ዳታዎችን በመሰብሰብ፣ለማደራጀትና ለመተንተን ከ16 ቢሮዎችና ከ6 ዞኖች መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል ፣ እንዲሁም መረጃ በአግባቡ እንዲደራጅ ተደርጓል ፣ አሁን ላይ የመተንተን ስራው ወደ ማለቁ ላይ ነው ፡፡እነዚህን ሶሽዮ ኢኮኖሚክ መረጃዎችን አሳትመን ከማሰራጨታችን በፊት የመረጃዎቹን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ዞኖችን እና ክልል ሴክተር መ/ቤቶች ባሉበት መድረክ ፈጥረን መግባባት ስንችል እናሰራጫለን ፡፡
መ/ኮ፡-ተቋማትን ከመደግፍ አኳያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ቢገልጹልኝ
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡-   በአንድ ዕቅድ በአንድ ሪፖርት መርህ መሰረት ሁሉም ቢሮዎች ዕቅዳቸውን ከመተግበር አኳያ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ 20 ቢሮዎችን በመዘዋወር ምልከታ ማድረግና መገምገም ችለናል ፡፡ቀጣይ መስራት ስላለባቸው የዕቅድ አካል ሆኖ ያልተከናወኑ ተግባራት ቀጣይ ላይ መተግበር እንዲችሉ በቅርበት የመደገፍ ስራ እየሰራን እንገኛለን ፡፡ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው ጊዜ እየተሰሩ መሆኑንና ፊዝካልና ፋይናንሺያል ስራዎች ያሉበትን ደረጃ በመመልከትም ቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እና ክትትል እያደረግን እንገኛለን ፡፡
መ/ኮ፡- አጠቃለይ የክልሉ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም በዋና ዋና መለኪያዎች ምን ይመስላል ? 
ወ/ሮ ቤቴልሄም ዳንኤል ፡-  ከግብርና ስራዎች አንጻር በአዝርዕት ሰብሎች 19 ሚሊዮን 890 ሺህ 492 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ችለናል ፡፤ እንዲሁም በተመሳሳይ በሆልቲ ካልቸር ሰብሎች 33 ሚሊየን 548 ሺህ 958 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል ፡፡ይህ በግብርና ምርታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የመሰብሰብ አቅማችን እያደገ መጥቷል ማለት ነው ፡፡ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ከማቅረብ አንጻር 35 ሺህ 762 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ችለናል ፡፡ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ለ34 ሺህ 6 መቶ 26 ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ፡፡ከኤክስፖርት ምርት አንጻር ወደ ውጭ በመላክ 4.9 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል ፡፡ በአጠቃላይ በ9 ወራት የሰበሰብነውን ገቢያችንን ስንመለከት 6 ቢሊየን 841 ሚሊየን 632 ሺህ 107 ብር ገቢ መሰብሰብ ችለናል ፡፡ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስንመለከት 64 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ፡፡ወርቅን ለብሄራዊ ባንክ ከማቅረብ አንጻር 108 ኪሎግራም ማቅረብ ተችሏል ፡፡ ከዕቅድ አንጻር ገና 46 ከመቶ ብቻ ተከናውኗል ፡፡በbቀጣይም እዚህ ላይ በትኩረት መስራት አለብን ፡፡ በአጠቃላይ እንደ ክልል አመርቂ ስራዎች ተከናውነዋል ፡፡ በቀጣይ ባልተከናወኑ ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ ይሆናል ፡፡
መ/ኮ፡- ለሰጡን ማብራሪያ ክልብ አመሰግናለሁ
ወ/ሮ ቤቴሌሔም ዳንኤል ፡- እኔም አመሰግናለሁ ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *