



ከኢትዮጵያውያን አርበኞች የሀገር ፍቅር እና ትጋትን ልንማር ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት 84ኛው የአርበኞች የድል በዓል እየተከበረ ይገኛል።
በመርሀ-ግብሩ ላይም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስሥላሴ በአርበኞች መታሰቢያ ድል ሀውልት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጨምሮ ፣ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ- ግብሩ ላይ ታድመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ድሉ የፋሽዝምና ቅኝ ግዛት እሳቤ ዳግም እንዳያንሰራራ ያደረገ ነው ብለዋል።
ይህንንም ብርቱ ተጋድሎ ለዓለም ያሳየንበት መታሰቢያ በአል መሆኑንም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያውያን አርበኞች የሀገርን ፍቅር እና ትጋትን በመማር ለሀገር እድገት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አሁን የኢትዮጵያን የእድገት ግስጋሴ ማቆምም ሆነ መግታት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያን በመወከል ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሰራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በበኩላቸው አርበኝነት ከሀገር ፍቅር የሚመነጭ ስሜት ነው ብለዋል።
እለቱ ለነጻነት እና ለብሔራዊ ክብር መስዋእት የከፈሉ የሚታወሱበት መሆኑን ገልጸው ለአሁኑ ትውልድም ለሀገር የተከፈለውን ዋጋ ልናሳውቅበት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርሶችን በመንከባከብ እሴት በመጨመር ከነሙሉ ክብራቸው አየጠበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም የአርበኞች ድል ሀውልትንም ባማረ መልኩ ትውልድ እንዲማርበት ተደርጎ አካባቢው መልማቱን ተናግረዋል።
የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ድሉ ኢትዮጵያ ራሷን ያጸናችበት የድል በአል መሆኑን ተናግረዋል።
በአሉን በሚመጥን መልኩ በተዋበ አካባቢ በመከበሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በአራት ኪሎ አካባቢ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ለበአሉ ድምቀት መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
ወጣቱ ትውልድ በሰላምና በልማት ግንባታ ስራዎች ላይ ይበልጥ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
