




የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ስርዓት የግብርና ግብአት ሽያጭ ፕሮግራም መርሃ ግብር አካሂዷል ።
በዚሁ በኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ስርዓት የግብርና ግብአት ሽያጭ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ግብኣት ሽያጭ ስርዓት የግብርና ግብኣት ፋይናንስ አሰራርን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት በአርሶአደሩ ምዝገባ መሠረት መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል ።
የኤሌክትሮኒክ የግብርና ግብዓት ሽያጭ በጎጊባ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አማካኝነት የሚከናወን መሆኑንም አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል ።
ይህ ለጎጊባ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የቁጠባ ባህልን የሚያዳብርና የብድር ስርጭትን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዘው አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ያለ ብድር ሙሉ በሙሉ ሽያጭ ይከናወናል ሲሉም ተናግረዋል ።
የኤሌክትሮኒክ የግብርና ግብኣት ሽያጭ አሰራር አሁን በተጀመሩ የፓይለት ወረዳዎች ውጤታማነቱ ታይቶ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ተግባራዊ እንዲደረግ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ደቡብ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ግርማሜ ጋሩማ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክ የግብርና ግብኣት ሽያጭ ስርዓት ከዛሬ ጀምሮ በተመረጡ ወረዳዎች እውን ይደረጋል ብለዋል።
ይህንን አሰራር ውጤታማ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል ስራ አጠናክሮ ያስቀጥላል ሲሉም አቶ ገርማሜ ተናግረዋል ።
ኤሌክትሮኒክ የግብአት ሽያጭ ሥርዓትን በማስመልከት የመወያያ ሰነድ በአቶ ተሰማ ሂርባዬ ቀርቧል ።
ኤሌክትሮኒክ የግብአት ሽያጭ ሥርዓት አርሶ አደሮች ያላቸውን ውስን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር የሚፈታ የዲጂታል አማራጭ ቴክኖሎጂ መሆኑን አስረድተዋል።
ለአርሶ አደሮች ጊዜ እና ወጪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፤ የፋይናስ አቅርቦትን ያሳልጣል፤ ወቅታዊ ሪፖርቶችን ለማግኘት እንደሚያስችልም የኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ስርአት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተሰማ ላፍቶ ተናግረዋል ።
የአትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል ግብርና ላይ ለውጥ ለማምጣት እና ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የፋይናስ አካታችነትን ለማስተዋወቅ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብኣት ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ የኤሌክትሮኒክ የግብአት ሽያጭ ትግበራ የአፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 27/2017 ን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የክልሉ መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ በጀት መመደቡንና አርሶአደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል ።
በሂደቱም የሚስተዋለውን ብክነት ለመቀነስና የፋይናንስ አሰራር ስርዓትቱን በማዘመን የወረቀት ኩፖን አሰራርን ለማስቀረት የኤሌክትሮኒክ ቫውቸር የግብርና ግብኣት ሽያጭ መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።
ይህም አርሶአደሮች በሞባይል ስልኮቻቸው አማካኝነት የግብርና ግብኣት ሽያጭ እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል ብለዋል አቶ አስራት አሰፋ።
የኤሌክትሮኒክ የግብአት ሽያጭ ሥርዓት በሙከራ ደረጃ በቤንሸኮ እና ካፋ ዞኖች በደቡብ ቤንች፣በጉራፈርዳ እና ጊንቦ ወረዳዎች ይጀመራል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት የኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ሽያጭ ወደ ተግባር መግባቱ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።
መመሪያውን ተከትሎም ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።
የኤሌክትሮኒክ የግብአት ሽያጭ ሥርዓት ፕሮግራም ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ ከፌዴራል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የገጠር ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።
በታጠቅ አበበ
