




ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞችን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን በኮንታ ዞን የአመያ ዙሪያ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ውጤታማ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ዳዕሞ እንደገለፁት በዚህ መርሐ-ግብር ከሚተከሉ ችግኞች መካካል አብዛኞቹ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ የቡናና ቅመማ ቅመም ችግኞች መሆናቸዉን ተናግረዋል።
ኃላፊው አያይዘውም እንደ ወረዳ የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በ2 ምዕራፎች በበልግና በመኸር እንደሚከናውን የተናገሩ ሲሆን በዚህም መሠረት በበልግ ተከላ ወቅት ከ975 ሺህ በላይ ችግኝ የሚተከል እንደሆነና በመኸር ወቅት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ማሳወቃቸውን
የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች በተደረገላቸው እንክብካቤና ጥበቃ አድገዉ ተጨባጭ ዉጤት እየታየባቸው መሆኑን የገለፁት አቶ ካሳሁን የአካባቢው ሕብረተሰብ ከተከላዉ ጎን ለጎን የእንክብካቤ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አክለዋል።
