ሪፖርታዥ
የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት በትኩረት ዕየተሠራ መሆኑን የፍትህ ቢሮ አስታወቀ
የክልሉ የሶስት ዓመት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የፍትህ ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የክልሉ ነዋሪዎች ከፍትህ አገልግሎት የሚጠብቋቸዉን ዉጤቶችን በበቂ ሁኔታ ማምጣት አልተቻለም፡፡ አሁንም በክልላችን በፍትህ ዘርፍ አገልግሎት ላይ ከህብረተሰቡ የሚነሱ እሮሮዎች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአገልግሎቱ የህብረተሰቡን እርካታ እና አመኔታ ማጣት የሚያመላክቱ መሆናቸው ይጠቀሳል ፡፡
በክልላችን ይህ ዘርፍ ከህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ውጤት ለማምጣት በሚያስችለው ልክ ለማምጣት የማሻሻል ስራ መስራት እጅግ አድካሚ እና ፈታኝ ቢሆንም ጊዜ የሚያሰጥ ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማሻሻል የዜጎችንና ነዋሪዎችን እርካታና አሜነታ ለመጨመር በክልሉ ፍትህ ዘርፍ ተቋማት አገልግሎት አሠጣጥ ረገድ የሚስተዋሉ ጉዳዮችን በጥናት በመለየት የክልሉ የሶስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ /ፍኖተ ካርታ/ በአስር ዋና ዋና አምዶች/የማሻሻያ እርምጃዎች ዙሪያ ተዘጋጅቶ በክልል ደረጃ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ተናግረዋል ፡፡
የፍትህ ዘርፉ የትራንስፎርሜሽን አምዶች ወይም የማሻሻያ እርምጃዎችም ተለይተው በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ እንደሚገኙም አቶ እሸቱ አብራርተዋል ፡፡ በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ ያሉ አምዶች ፡-
1ኛ. የመሰረተ ማህበረሰብ የፍትህ አገልግሎት በክልላችን በተደረገ ዳሰሳ ጥናት ህዝብን መሰረት ያደረገ ማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ አገልግሎት ከመደበኛ የፍትህ አገልግሎት ጋር በአማራጭ እና በድጋፍነት አጣጥሞ ማስኬድ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ተለይቷል፡፡ በተጨማሪም በክልላችን ከባድና ዉስብስብ የሆኑ የህግ ጉዳዮች በፍትሀዊነትና ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን በማህበረሰቡ መካከል ለማምጣት በሚያስችሉ መልኩ በክልላችን በሁሉም ዞኖች የአከባቢ ባህልን መሰረት ባደረጉ ዕዉቀቶች እልባት እያገኙ መሆናቸዉን ለመገንዘብ መቻሉንም አቶ እሸቱ ገልጸዋል፡፡ህብረተሰብን መሰረት ያደረገ የፍትህ አገልግሎት የህግ መሰረት ኖሮት በተደራጀ መንገድ በአማራጭነት ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ምቹ መደላድሎችን መፍጠር አስፈሊጊ መሆኑ በመታመኑ በዚህ አምድ ስር 7(ሰባት) ዋና ዋና ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱንም ገልጸዋል ፡፡
የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እዉቅና ለመስጠት የሚያስችሉ ረቂቅ አዋጅ በቢሮዉ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ አዋጅ ቁጥር 35/2016 በመሆን ፀድቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባህላዊ ዳኝነት ሥርዓቱን ለማደራጀት እና እውቅና ለመስጠት በማሰብ ከክልሉ ከተለያዩ መዋቅሮች ከተውጣጡ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት በቅርበት ለሚከታተሉና ለሚደግፉ ከሁለም የክልሉ ወረዳ /ከተማ አስተዳደር ፍ/ቤቶች ለተዉጣጡ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በአዋጁ ዙሪያ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ባመቻቸዉ መድረክ ቢሮዉ ስልጠና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተግባቦት ከተፈጠረ እና ለሚመለከታቸዉ አካላት የግንዛቤ ስልጠና በህጉ እና ስለ አገልግልቱ ከተሰጠ በኃላ በክልሉ ዉስጥ ባሉት በ252 ቀበሌያት ላይ የባህላዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የማቋቋም እና አገልግሎት ሰጪ ዳኞችን የመመልመል ስራ ተሰርቷል ብለዋል ፡፡ በቀሪ ቀበሌያትም ላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የማደራጀት እና አገልግሎት ሰጪ አካላት የመመልመል ተግባር እንዲሁም በክልል ደረጃ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ ጽ/ቤት በክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ስር ስለሚደራጅበት ሁኔታ ከፍ/ቤቱ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ ከባህላዊ ዳኝነት አገልግሎት ጎን ለጎን ህብረተሰቡ በአማራጭ የፍትህ አገልግሎት የሚያገኝበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቀድሞ የነበረዉን የማህበራዊ ፍ/ቤት አደረጃጀትና አሰራር ማነቆ ፈትሾ ማስተካከል አስፈሊጊ በመሆኑ የማህበራዊ ፍርድ ቤት አዋጅ ተዘጋጅቶ በክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ አዋጅ ቁጥር 41/2016 ሆኖ ፀድቆ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁም መሰረት በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በኩል ለማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኞች በሰፊዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመስራት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
2ኛ. የፍትህ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎችን ማጥራት በዘርፉ ያሉ የባለሙያዎች የሙያ ብቃት እና ስነ ምግባር ጥራት መጓደል ለህብረተሰቡ የእርካታ ማጣት ምንጭ በመሆኑ በክልሉ የተደራጀ እና የተጠቃለለ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች የማጥራት ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡ በዚሁም መሰረት አራት ዋና ዋና ተግባራት ለማከናወን ዕቅድ የተያዘ ሲሆን በመደበኛነት የፍትህ ዘርፍ ተቋማት ከሚያከናዉኗቸዉ የማጥራት እርምጃዎች በተጨማሪ የትራንስፎርሜሽን ተግባሩን ለማሳካት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰራ ይገኛል ሲሉ አቶ እሸቱ ገልጸዋል፡፡
3ኛ. በፍትህ ዘርፍ ተቋማት ያደገ እና ውጤታማ የኢንፎርሜሽን ኮሚውኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም መተግበር በአሁኑ ወቅት በዘርፉ አጠቃቀም ልምድ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ግልጽና እና ጊዜዉን የዋጀ የፍትህ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉ በመሆኑ የፍትህ ዘርፍ አገልግሎትን በቴክኖልጂ ማስደገፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አይነተኛ መፍትሄ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡ በዚሁም መሰረት ይህንን አምድ ለመተግበር እንደ ክልል 15 (አስራ አምስት) የሚሆኑ ዝርዝር ተግባራት ታቅደው እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡
4ኛ. የወንጀል፣ የአስተዳደርና ፍትሐ ብሔር ፍትህ ሥርዓት ፕሮግራም፡ በአዲስ አስተሳሰብ. በወንጀልና በፍትሀብሔር ፍትህ አስተዳደር ረገድ በተግባር የሚከናወኑ ሂደቶች ከጊዜዉ ጋር የማይሄዱ በመሆናቸዉ ምክንያት የፍትህ ስርዓቱ ዉጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደሩ በእነዚህ ህጎች ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ተከትለን በክልላችንም በበርካታ ጉዳዮች ላይ የማሻሻያ ስራ ለመስራት 19 (አስራ ዘጠኝ) ተግባራት ታቅደው እየተከናወኑ እንደሚገኙም አቶ እሸቱ ተናግረዋል ፡፡ በተጨማሪም በክልላችን የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግ ከመንግስታዊ የአስተዳደር ተቋማት ከሚደርስ አስተዳደራዊ በደል የሚመነጩ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መፍቻ መሳሪያ መሆኑ ታምኖ የአስተዳደር ስነ ስርዓት ህግን አውጥቶ በማስጸደቅ ቢሮዉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል፡፡
5ኛ. የተጠናከረ ንቃተ-ሕግ እና የሕግ ድጋፍ በክልላችን የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ዱሞኪራሲን በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ግለሰቦች መብታቸዉን አዉቆ ከመጠቀም ባሻገር ግዴታቸዉን በአግባቡ አዉቆ እንዲወጡ ለማስቻል ውጤታማ በሆነ የሕግ ትምህርት እና የንቃተ ሕግ ዘመቻ የዜጎችን መሰረታዊ የንቃተ-ሕግ ደረጃ ማሳደግ አስፈሊጊ መሆኑ በመታመኑ፣ እንዲሁም በክልሉ መሰረታዊ የሕግ እውቀት እና ገንዘብ ከፍለው የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለማግኘት የማይችሉ አቅመ ደካማ ዜጎች የሕግ ድጋፍ የሚያገኙበትን እድል ለማመቻቸት ስምንት ተግባራት ታቅደው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
6ኛ. ዘመናዊ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ማስፋፋት እነዚህ የሙግት መፍቻ ስርዓቶች በክልላችን በፍትሀብሔራዊ እና ገንዘብ ነክ ክርክሮች አኳያ በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታየውን የመዛግብት መጨናነቅ እና የውሳኔ መዘግየት የሚቀንሱ ከመሆናቸዉም በላይ ለሙስና የመጋለጥ ዕድላቸውም አነስተኛ በመሆኑ በዚሁም ረገድ ተግባራት ታቅደው እየተከናወኑ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
7ኛ. የተሻለ የጎንዮሽና የተዋረድ የፍትህ ዘርፍ ተቋማት ቅንጅት በክልሉ ዉስጥ አንኳር የፍትህ ዘርፍ ችግሮች ዉስጥ አንዱ በፍትህ ዘርፍ ዉስጥ ባሉ ተቋማት መካከል ያለዉ ዉጤታማ የተዋረድ እና የጎንዮሽ ቅንጅት መጓደል በመሆኑ ዉጤታማ ቅንጅታዊ ስራ በመስራት የፍትህ አገልግሎትን ለማሳለጥ አምስት ዋና ዋና ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል ፡፡
8ኛ. የፍትህ አካላት ተቋማት ያላቸው ተደራሽነትን ማሳደግ የፍትህ ዘርፍ ተቋማት አሁናዊ ክፍተቶች መካከል አንዱ የፍትህ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ አለማድረግ ሲሆን በዚሁም ረገድ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የፍትህ ዘርፍ ተቋማት በማዕከል ደረጃ ከሚሰጡት የፍትህ አገልግሎት በተጨማሪ የክልሉ ህብረተሰብ ከስራዉ ሳይፈናቀል ለወጪና እንግልት ሳይዳረግ በአቅራቢያቸዉ የፍትህ አገልግሎትን እንዲያገኙ ለማድረግ ቋሚ ምድብ ጽ/ቤቶችን በማደራጀትና በተዘዋዋሪ ከማዕከል ተንቀሳቅሶ የፍትህ አገልግሎትን ለመስጠት ታቅዶ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እየተሰራ ነው፡፡
9ኛ. ተገቢና ዉጤታማ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ያለ ዉጤታማ የህብረተሰብ ተሳትፎ የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የማይሳካ በመሆኑ በሚታቀዱ የዘርፉ ዕቅዶች፣ የአፈጻጸም ግምገማዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ነጻ የሆነ የህብረተሰብ አስተያየት መስጫ ሥርዓት፣ በወንጀል ጉዳዮች ምስክርነት እንዲሁም የአካባቢዉን ሠላምና ጸጥታ በማስከበርና በመደገፍ፣ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች አማካይነት ፍትህን በመስጠት እና በሌሎች ጉዳዮች ህብረተሰቡ ተሳትፎ በሚያደርጉባቸዉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት 9(ዘጠኝ) ዝርዝር ተግባራትን የያዘ ዕቅድ ታቅዶ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
10ኛ. የፍትህ ዘርፍ ተቋማት አደረጃጀትን ማስተካከልና ዘርፉን ሳቢና ታማኝነት የተቸረዉ ማድረግ፣ የፍትህ ዘርፍ ስራዉ በባህሪ ዉስብስብ፣ድግግሞሽ ያለበትና አመዛዛኝነትን የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከቅጥር ጀምሮ የሰው ሀብቱን ማሟላት አስቸጋሪና ወደ ፍትህ ተቋማቱ የገቡ ልምድ ያላቸዉ ሰራተኞችም በመሰላቸትና በሌሎች አካባቢ በተሻለ ገንዘብ ትንሽ ጉልበት አውጥቶ መስራት ከመፈሇግ አንጻር የማይቆዩና የሚኮበሌለ በመሆኑ፣ ዘርፉን ዉስጥ ላሉትና ከዉጭ ለሚመጡ አመራሮችና ሰራተኞች የሚስብና የሚያነሳሳ በማድረግ ልምድና ዕዉቀት ያላቸዉን ባለሙያዎችን ለማቆየት አስራ አንድ ዝርዝር ተግባራትን የያዘ እቅድ ታቅዶ እየተከናወነ ይገኛል ሲሉም አቶ እሸቱ አስረድተዋል ፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ከላይ በተጠቀሱት የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያ አምዶች መሰረት ተደርጎ የተዘጋጀዉን የክልሉን ፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት በክልሉ ዉስጥ በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለዉን ችግር በመፍታትና መሰረታዊ ለዉጥ በማምጣት በአገልግሎቱ የክልሉን ህብረተሰብ እርካታና አመኔታ ለማምጣት የህብረተሰቡ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ እሸቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በታጠቅ አበበ
የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት በትኩረት ዕየተሠራ መሆኑን የፍትህ ቢሮ አስታወቀ
