የአፍሪካን የመልማት አቅም ወደ ውጤት የምንቀይርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Spread the love

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዘላቂ የግብርና ልማዶችን፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ለአርሶ አደሮች የገበያ ተደራሽነትን በማጠናከር የአፍሪካን የመልማት አቅም ወደ ውጤት የምንቀይርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ገለጹ።

‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ብራዚል ይገኛሉ።

‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ሰፊ ፋይዳ ካለው ጉባዔ ተሳትፏችን ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ከብራዚል ምክትል ፕሬዚደንት እንዲሁም የኢንዱስትሪና ልማት ሚኒስትር ጀራልዶ ሮድርጌዝ አልካሚን ጋር አከናውነናል ብለዋል።

‎በውይይቱ ምክትል ፕሬዚደንት ጀራልዶ ሮድርጌዝ አልካሚን የኢትዮጵያን ፈጣን እድገትና በጥሩ መሰረት ላይ የሚገኘውን የሀገር ውስጥ ምርት መነቃቃትን ማድነቃቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት በትብብር እየተገበሯቸው ከሚገኙ ስራዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት ጠንካራና ዘመናዊ የአቬሽን ዘርፍ ሀገራቸው ብራዚል አብሮ የመስራት ሰፊ ፍላጎት እንዳላትም ጠቅሰዋል።

‎‎‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ኢትዮጵያ እና ብራዚል ከዚህ ቀደም በግብርና፣ የደን ልማት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም የአሲዳማ አፈር አጠቃቀም ፕሮጀክቶችን በትብብር የመስራት ስምምነት እንዳላት አንስተዋል።

በውይይታችን ስትራቴጂያዊ ትብብሮችን በተለይም በግብርና፣ ዘላቂ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ ተቀራርበን ለመስራት የሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገናል ብለዋል።

‎የቀደሙትንና የቀጣይ የጋራ ስራዎችን በባለብዙ ወገን ትብብርንና ሌሎች ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ አሰራሮችን ለመተግበር ከምክትል ፕሬዚደንት ጀራልዶ ሮድርጌዝ አልካሚን ጋር አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን‎‎‎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *