




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የግብርና ቢሮ እርሻ ዘርፍ ከሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSPR) ጋር በመተባበር ከዞንና ከወረዳ ለተወጣጡ የግብርና ባለሙያዎች በሰብል አመራረት ፓኬጅ ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነው ።
ስልጠናው በሰብል አመራረት ፓኬጅ ፣በዋና ዋና የብርዕና አገዳ ሰብሎች በሽታ መከላከል ፣አሲዳማ እና ኮትቻ አፈር ልማት ዘዴ፣የACC እና FPC አተገባበር፣ጽንስ ሀሳብ እና ኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ላይ ዓላማ ያደረገ ነዉ።
የስልጠና መድረኩን ያስጀመሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ እንደሀገር በመኸር ሰብሎች አዲስ ፓኬጅ አሠራር ላይ የተከለሰዉን መነሻ በማድረግ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ የፓኬጅ ጥንቅር ግምገማ ተደርገው ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
አሁን የበልግ እርሻ ማጠቃለያ ምዕራፍ እና ለመኸር እርሻ በቂ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት በመሆኑ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ኃላፊው።
በክልሉ በቂ የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲያስችል አዳዲስ በምርምር የወጡ እሳቤዎችን ተግባራዊ ማድረግ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻል እንደሚገባም ነው አቶ አሸናፊ ክንፉ የተናገሩት።
በክልሉ በፊት የሰብል ምርትና ምርታማነት ልጨምሩ የሚችሉ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም መጠን ዝቅተኛ እንደነበር ያነሱት ኃላፊው ቀጣይ መጠኑን መጨመር እንዲያስችል በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።
በዚህም በአዝርዕት ሰብሎች አመራረት ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ይበልጥ ለማሻሻል እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
ስልጠናው በሰብል አመራረት ዘዴ ላይ የሚስተዋለውን የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ማሻሻል እና የአፈር አሲዳማነት ችግር በዘላቂነት መቅረፍ እንዲያስችል የአፈር ለምነት ማሻሻያ ላይ በተለይም በኖራ አጠቃቀም፣ኮምፖስት፣ቨርም ም ኮምፖስት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመከናይዘሽን እና የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አጨዳ ድረስ ባሉ ሂደቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አቶ አሸናፊ ክንፉ ተናግረዋል።
በክልሉ በቂ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ከማረጋጋት በተጨማሪ ወቅቱ የመኸር የእርሻ ወቅት በመሆኑ ባለሙያዎች አዳዲስ በምርምር የወጡ እሳቤዎችን በመያዝ ለዘርፉ ውጤታማነት መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።
ስልጠናው ለዞንና ለወረዳ ባለሙያዎች የሚሰጥ በመሆኑ አሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመረዳት ወደታች በማውረድ በልማት ጣቢያ የሚገኙ ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና አርሶ አደሩን በማነቃነቅ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ትኩረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
በቦንጋ ማዕከል እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠና ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ቀጣይ በሚዛን አማን እና በአመያ ማዕከል ከዞንና ከወረዳ ለተወጣጡ ለዘርፉ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጥ መሆኑም ተመላክቷል።
በፍቅር ከበደ
