የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጥ በርካታ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን ባለሙያዎችና ባለይዞታዎች ገለፁ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ፣ በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም (CALM) ድጋፍ ሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ምዝገባ፣ ማረጋገጥና የባለቤትነት ማረጋገጫ የካርታ ስርጭት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።

አርሶአደር ገባነሽ ኬሮ እና አንጉቱ ኡራቾ በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ፣ የአንጊዮ ቆላ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆን፥ ማሳቸው የ2ኛ ደረጃ የገጠር መሬት ልኬት ተከናውኖ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መቀበላቸውን ይናገራሉ።

የይዞታ ማረጋገጥ ሂዴቱ አሳታፊ፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓት እና የተሟላ ግልጽነት የነበረው እንደነበረ የሚገልጹት አርሶአደሮቹ ተግባሩ ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረውን የድንበር ግጭት ለማስወገድ እንዲሁም መሬትን ለሶስተኛ ወገን በህጋዊ መንገድ በክራይ ለማስተላለፍ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የመሬት ማረጋገጫ ካርታውን በዋስትና በማስያዝ ከገንዘብ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ብድር በመውሰድ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳለው የገለጸው ሌላኛው የቀበሌው አርሶአደር ቆጭቶ ሀሰን ለተግባራዊነቱ የመንግሥት ድጋፍ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የይዞታ ማረጋገጥ ተግባር የአርሶአደሩን በመሬት የመጠቀም መብትንና ባለቤትነትን በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ነውጰበኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የካልም-ፕሮግራም የሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ልኬት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ግርማ የገለጹት።

ክልሉ ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ መልካ-ምድራዊ አቀማመጥና የደን ሽፋን ያለበት በመሆኑ የመሬት ምዝገባ መረጃ ከአየር ላይ ፎቶግራፍ በተጨማሪ ዘመኑ የደረሰበትን የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ በመጠቀም ለማሰባሰብ የሙከራ ስራ ተከናውኖ አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት በመሆኑ ቀጣይ ለማስፋት በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ክልሉ አዲስ በመሆኑ ሰፊ የመሬት አስተዳደር ስራዎች ከፊት እንደሚጠበቅበት የገለጹት አቶ ካሳሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባሩን ከሚደግፉ አካላት ጋር በመሆን የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በክልሉ የግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አበበ ታደሰ በበኩላቸው፥ በፕሮግራሞች ድጋፍ በ17 የክልሉ ወረዳዎች የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን በመጠቆም ከነዚህም ውስጥ የ14 ወረዳዎች መረጃ ወደ ብሄራዊ የገጠር መሬት መረጃ ቋት በማስገባት የባለቤትነት ካርታ ስርጭት መከናወኑን ገልጸዋል።

አጠቃላይ የክልሉን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም የሚያስተዳደር አዋጅ በክልሉ ግብርና ቢሮ አማካኝነት ተዘጋጅተው ለሚመለከተው ክፍል መተላለፉን ያብራሩት አቶ አበበ አዋጁ በምክር ቤት ፀድቆ በስራ ላይ ስውል የአርሶአደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነም ነው የገለጹት።

መረጃቸው በብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ቋት ከተመዘገቡት ባለይዞታዎች ውስጥ 678 አርሶአደሮች የማረጋገጫ ካርታ በማስያዝ የብድር ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ያብራሩት አቶ አበበ አዱሱ አዋጅ ባለይዞታዎች ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የሚገናኙበትን አሰራር በመዘርጋት የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነውም ብለዋል።

የሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ምዝገባ ስራው በገጠር መሬት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ አርሶአደሮች ሙሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማሳቸው ላይ በማድረግ ምርታማነትን እንዲያሳድጉ እንደሚረዳቸው የገለጹት አቶ አበበ በክልሉ በ17 ወረዳ የተጀመረውን ተግባር በሌሎች አከባቢዎችም ቀጣይ ለማስጀመር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *