



በፎረሙ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እና ተጋባዥ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን በመስጠት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመቅረፍ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ።
በአንድ አካባቢ በህብረተሰቦች መካከል የሚፈጠረው ግጭት እየተባባሰ ሌላ የከፋ አደጋ እንዳያስከትል አመራሩ በሰከነ መንገድ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ማስቀጠል ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ ግጭት ቀስቃሽ አካላት ላይ ህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም በተሳታፊዎች ተነስቷል።
በቀሩቡት ሁለት ሪፖርቶችና በተነሱት ሀሳቦች ላይ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኦሞድ በሁለቱም ክልሎች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የፎረሞች መካሄድ ዘላቂ የሆነ የህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመለሱበትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው።
በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመቅረፍ አመራሩ ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ፎረሞችን ለዘለቄታ ሰላም ማረጋገጫ አድርጎ መጠቀም ይኖርብናልም ብለዋል።
በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በእርቅ የመፈጸሙ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም በመግለጽ አጥፊዎች በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።
በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ሁኔታም ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ መድረኩን ሲያጠቃልሉ ግጭቶችን በመቅረፍ የህዝብን ጥቅም መሠረት ያደረገ የፎረም ውይይቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ባህላዊ የእርቅ እሴቶችን በማጎልበት ሰላም ማስፈን እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትሩ አጥፊዎች በህግ የሚጠየቁበትን አሰራር ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።
ግጭት በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ፈጥኖ በወደ ስራ በማስገባት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም ሲሉ ተናግረዋል ።
ግጭቶችን መፍታት በሚቻልበትና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ትኩረት ያደረገው 2ኛው ዙር የደቡብ ምዕራብ ህዝቦችና የጋምቤላ ህዝቦች የሰላምና የልማት ፎረም የህዝቡን ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በመግባባት ተቋጭቷል።
በታጠቅ አበበ
