በክልሉ የትምህርት ምዘና እና የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው- አቶ አልማው ዘዉዴ

Spread the love

”የዘመነ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም ሀገራዊና ክልላዊ የፈተና አስተዳደር የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘዉዴ እንዳሉት፤ በትምህርት ሴክተር ሪፎርም ከተደረጉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የፈተና ምዘና እና የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ማዘመን ዋነኛው ነው።

በክልላችን የትምህርት ምዘና እና የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ለማዘመን የትምህርት አመራሩና ማህበረሰቡ ዘንድ በተሰጠው ትኩረት መሠረታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ነው አቶ አልማው ዘዉዴ ያስረዱት።

የሀገር ዓቀፍ እና ክልል ዓቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችን በኩርጃና በስርቆት ለማለፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀርተው በራስ ሰርተው እና ደክመው ውጤት የሚያመጣ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።

ለሀገራዊ ዘላቂ ብልጽግና እና ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችል ትውልድ ለመፍጠር በክልላችን ባለፉት ዓመታት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተናዎችን መስጠትና እና የትምህርት ምዘና ሥርዓት የማዘመን ሥራዎች ላይ በትኩረት ሲከናወኑ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ጊዜያት ከ1ሺህ 1መቶ 11 በላይ ተማሪዎች በሚዛን እና ቦንጋ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተና በኦንላይን ፈተና እንዲወስዱ በማደረግ የተሻለ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት።

አቶ አልማው በዘንድሮ ዓመት በክልላችን ባሉት በአራቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 19127 የሚጠጉ ተማሪዎችን ሀገራዊ መልቀቁያ ፈተና ለመስጠት የቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቀ መሆናቸውን ከእዚህ 2690 ተማሪዎች በኦንላይን ፈተና የሚወስደዉ መሆኑን ጠቁመው የተጀመረው ስራ የሚፈልገውን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

ዘንድሮ በክልሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመዝግቡ እየተሰራ ካለው በተጨማሪ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ማለፊያ ፈተና ለመስጠት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛልም ብለዋል አቶ አልማው ዘዉዴ።

የ2017 ዓ.ም ክልላዊና ሀገራዊ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት የእስካሁኑ የተግባራት አፈጻጸም ሰነድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትልና የመማር ማስተማር እና የምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ በኩል እየቀረበ ይገኛል።

በመድረኩ የክልሉ አስተባባሪ አካላትና ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎች፣የዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንዲሁም የክልልና የዞን የዘርፉ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *