


በሚዛን አማን ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ እንዲፋጠን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።
ከነዋሪዎቹ መካከል መቶ አለቃ ተስፋዬ ናትናኤል፥ የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ያለውን የኮሪደር ልማት የእግረኛን መንግድ በማስፋትና የመናፈሻ አገልግሎትን ማስፋት ያሰቻለ ሰው ተኮር ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ልማቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲፋጠን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታውቃዋል።
እስከ አሁን የተጠናቀቁ የኮሪደር ልማት ስራዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማቀላጠፍ የተሽከርካሪ አደጋን መቀነስ እንደሚያስችል አስተያየቱን የሰጠው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ታከለ ገብረማሪያም ነው።
ከተማዋን ንጹህ፣አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተጀመው የኮሪደር ልማት በተሳለጠ ሁኔታ እንዲፋጠን የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ተናግሯል።
ወጣት ኤርሚያስ አበበ በበኩሉ፥የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጿል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ ፤ በከተማዋ ከተጀመረው የአንድ ኪሎሜትር የኮሪደር ልማት ስራ የጎርፍ መፋሰሻ፣ የአረንጓዴ ልማት እና የእግረኛ መንገድ ስራው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ሥራ ኅብረተሰቡ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፥የተጀመሩትን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ቀጣዩን የኮሪደር ልማት ምዕራፍ ለማስጀመር ከከተማው ኅብረተሰብ ጋር በመቀናጀት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
