ሪፖርታዥ

Spread the love

የአውሮፓ ህብረት ደንብ ከደን ጭፍጨፋ ነፃ የሆኑ ምርቶች (EUDR) በአውሮፓ ኅብረት ገበያ ላይ የሚቀርቡ ምርቶች ለደን መጨፍጨፍ አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ ለማረጋገጥ ያለመ ደንብ ነው።


ደንቡ ሰባት ቁልፍ ምርቶች እና ተዋጽኦዎች ከደን መጨፍጨፍ የፀዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የንግድ ድርጅቶች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መሆኑም ተመላክቷል።
ደንቡ የአውሮፓ ህብረት አረንጓዴ ስምምነት አካል ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ለአለም አቀፍ የደን ጭፍጨፋ እና የደን መራቆት የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ለመቀነስ ያለመ ነው።
ደንቡ ሰባት ቁልፍ ምርቶችን ሚያጠቃልል ሲሆን እነሱም ፡- አኩሪ አተር፣ የዘንባባ ዘይት፣ ቡና፣ ኮኮዋ፣ ከብቶች፣ ጎማ እና እንጨት እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን ያጠቃልላል።
ንግዶች ለገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች ከደን ጭፍጨፋ ጋር ያልተያያዙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ አደጋዎችን መገምገም እና የመቀነስ እርምጃዎችን መተግበር እንደሚጠበቅባቸው ደንቡ ይደነግጋል።
የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸው ከደን ጭፍጨፋ የፀዱ እና የምርት ሀገሪቱን ህግ በማክበር የሚመረቱ መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው።
የEUDRን ደንብ ማክበር አለመቻል የገንዘብ ቅጣት፣ ምርቶችን መውረስ እና ከአውሮፓ ህብረት ገበያ ጊዜያዊ መገለል ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
27 ሀገራትን በአባልነት በመያዝ በኣዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ ደንብ በማውጣት ተፈጻሚ እንዲሆኑ እየሰራ የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ያዘጋጀው ደንብ በሀገራችንም ተፈጻሚ ሆኖ ዜጎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈለጋል ፡፡
(EUDR) በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራው አውሮፓ ህብረት ሀገራት ደንብ ወደ ሀገራቱ የሚገቡ ምርቶች ደንን ከመጨፍጨፍ በመታደግና ደንን በመጠበቅ የሚገኙ ሰብሎች በሀገራቱ ገበያ ውስጥ እንዲቀላቀሉ የሚደነግግ ስለመሆኑ የናቡ ኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክልል አስተባባበሪ አቶ አሳዬ አለማየሁ ይገልጻሉ፡፡
ዓለም በአንድ መንደር በሆነችበት ሁኔታ የሚወጡ ህጎች በቀጥታ ከሀገራቱ ጋር ህብረት ባላቸው ሀገሮች ተፈጻሚ የሚሆን ነው ሲሉም አቶ አሳዬ ተናግረዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2023 የወጣው የአውሮፓ ሀብረት ደንብ ደንን በመጨፍጨፍ የሚመጡ ምርቶችን የሚከለክል ስለመሆኑም አብራርተዋል ፡፡ሁለት ዓመት የሞላው ይኸው ደንብ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመሆኑም አቶ አሳዬ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያደረገች ያለው የማይበገር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያላት በመሆኑ በሀገሪቱ የሚመረተው ቡና በዛፎች ጥላ ውስጥ የሚመረት በመሆኑ ይህንን በማስጠበቅ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና አልሚ ባለሀብቶችን የወጣው ደንብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውም አቶ አሳየ ዘርዝረው አስረድተዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት በወጣው ደንብ መሰረት ቡናን ጨምሮ 7 የተለያዩ ሰብሎችን በደን ውስጥ መመረታቸውን በማረጋገጥ ወደ ሀገራቱ በማስገባት ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደነግግ ሲሆን በዋናነት ኢትዮጵያ ቡናን ወደ አውሮፓ ሀገራት እንደምትልክና በዚህም ከደን መመረቱን በማረጋገጥ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችልም ደንቡ ይደነግጋልም ብለዋል፡፡
ክልላችን ሁለት ባዮስፌሮችና ብሔራዊ ፓርኮች ያሉት በመሆኑ ቡናን በደን ውስጥ ስለማምረታችን ማስረጃዎች መሆናቸውንና ከዚህም ውጭ ህጋዊ ሆኖ ስለመመረቱ፣ የሀገሪቱን ህግ የተከተለ ስለመሆኑ፣ ሰብዓዊ መብት የጠበቀ ስለመሆኑና የይዞታ ካርታ ስለመኖሩ አመላካች መረጃዎችን ህብረቱ የሚፈልግ በመሆኑ አርሶ አደሩና አልሚው ባለሀብት በህጉ መሰረት ተጠቃሚ ለመሆንም እነዚህንና ሌሎች መረጃዎችን ማሟላት እንደሚገባቸውም አስረድተዋል፡፡
ለሀገራችን በተለይም ለክልላችን ቡናን ኤክስፖርት ሚያደርጉ አልሚ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች የሚጠበቀውን መስፈርት በማሟላት ገበያውን ሰብሮ በመጠቀም ኢኮኖሚን ማሳደግ ትኩረት በመስጠት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አቶ አሳየ አብራርተዋል፡፡
ከአውሮፓ ህብረት ሀገራት ውጭ ሌሎች አማራጭ ገበያዎች ቢኖሩም ለሀገራችን በመሰረታዊነት የሚጠቅመው በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መሳተፉ እንደሆነም አቶ አሳየ ገልጸዋል፡፡
በሌሎች ሀገራት የተሻለ የገበያ አማራጭ ቢኖርም ከአውሮፓ ሀገራት ውጭ ወደ ገበያው መቀላቀሉ ጊዜያዊ ጠቀሜታ ይኑረው እንጂ ዘለቄታዊነት የለውም ስሉም ገልጸዋል ፡፡
በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ በተለይ በቡና ሰብል ወደ ገበያው አለመቀላቀሉ በተለያዩ መንገዶች ሀገሪቱ ተጎጂ ሊያደርጋት እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል ፡፡
አርሶ አደሮችና አልሚ ባለሀብቶችም ዘላቂ ተጠቃሚነት ያው በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ባሉ ገበያዎች ገብቶ ተወዳዳሪ መሆን ሲቻል እንደሆነ ያስረዱት አቶ አሳዬ በየደረጃው ባለድርሻ አካላት ቡናን በጥራትና ደንን ጠብቆ በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አጽንኦት በመስጠት ጠይቀዋል፡፡
እንደክልላችን ደንቡ በፈረንጀቹ 2025 መጨረሻ ላይ ተፈጻሚ ስለሚሆን ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ካለው ፋይዳ አኳያ በተለይ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አቶ አሳዬ ጠይቀዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግስት መዋቅሮች፣የግብርና ተቋማት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ህብረት ስራ ማህበራት፣ አልሚ ባለሀብቱና ሌሎች አካላት ከወዲሁ በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋልም ሲሉ አቶ አሳዬ ጨምረው ጠይቀዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ አርሶ አደሮች፣አልሚ ባለሀብቱና ሀገሪቱ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉም ከክልሉ ግብርና ቢሮ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ጋር በመተባበርም ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንም አቶ አሳዬ አስረድተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *