የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love

ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ ሥር አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣  የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋ፣ የዳዉሮና የቤንች ሸኮ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳዩ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢዎቻችን አድርሰናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከክልላችን ዞኖች አንዱ የሆነውን የሸካ ዞንን እንቃኛለን፡፡

መልካም ንባብ!

የሸካ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ውስጥ ከሚገኙ ስድስት  ዞኖች አንዱ ሲሆን በሶስት ወረዳዎች፣ ሁለት ከተማ አስተዳደሮችና 63 የቀበሌ አስተዳደሮች (57 የገጠርና 6 የከተማ ቀበሌዎች) የተዋቀረ ነው፡፡ ሸካ ዞን በደቡብ ከቤንች ሸኮ ዞን፣ በምዕራብ ከጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን፣ በሰሜን ከኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦራ ዞን እና በምስራቅ ከካፋ ዞን  ጋር የሚዋሰን ሲሆን የዞኑ ዋና መቀመጫ ቴፒ ከተማ ሲሆን ከተማው ከክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞችም አንዱ ነው።

የ1999 ዓ.ም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትን መሠረት በማድረግ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ባደረገው ትንቢያ በ2016 የበጀት ዓመት የዞኑ ህዝብ ብዛት 339,942 (172,604 ወንድ እና 167,338 ሴት) እንደሆነ ይገመታል፡፡

የተለያዩ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በዞኑ ውስጥ ተፈቃቅረውና ተቻችለው የሚኖሩ ሲሆን ሸካቾ፣ ማጃንግና ሸኮ የዞኑ ነባር ብሔረሰቦች ናቸው።

የዞኑ አጠቃላይ ቆዳ ስፋት 238 ሺህ 750 ሄክታር ነው። የአየር ንብረቱ ደጋና ቆላ በብዛት የሚታይበት ሆኖ በሀገራችን በዩኒስኮ ከተመዘገቡት የባዮሰፈር ሪዘርቮች አንዱ በሸካ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህም 55 ሺህ 250 ሄክታር የሚሸፍን የሸካ ጥብቅ ደን ነው። በጥብቅ ደኑ ውስጥም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ሀገር በቀል የዛፍ ዓይነቶችና በርካታ እፅዋትና የዱር እንስሳት ይገኙበታል።

በርካታ ለአለም ገበያ የሚቀርቡ የኤክስፖርት ምርቶች ማለትም ቡና ፣ ሻይ ፣ ማርና ቅመማቅመም (ዝንጅብል ፣ኮሮሪማ ፣ጥምዝ፣ሄልና ቁንዶበርበሬ) በስፋት በዞኑ ይመረታሉ። የፍራፍሬ ልማትም አቮካዶ ፣ማንጎ፣ሙዝ፣ፓፓያና ሌሎች የፍራፍሬ  አይነቶችም በዞኑ በብዛት ይገኛሉ።

የዋና ዋና ምርቶች የማሳ ሽፋንን በተመለከተ 86 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 66 ሺህ 930 ሄክታር ምርት ይሰጣል። 5 መቶ 67 ሄክታር መሬት በሻይ ምርት የተሸፈነ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ምርት እየሰጠም ይገኛል። እንዲሁም 5ሺህ 6መቶ 77 ሄክታር መሬት በተለያዩ ቅመማቅመም ተሸፍኗል። በፍራፍሬም ከ1ሺህ 5መቶ ሄክታር በላይ መሬት ተሸፍኗል። ከ33ሺህ ሄክታር በላይ ማሳም በእንሰት የተሸፈነ ነው።

በዞኑ ውስጥ ወደ 46 የሚጠጉ የግብርና ኢንቨስትመንቶች በቡናና ቅመማቅመም ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚገኙ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የኢትዮ አግሪ ሴፍት ቡና ልማት፣ ኃይሌና አለም ቡና ልማት እና ኢስት አፍሪካ የሻይ ልማት በግዙፍነታቸው የሚታወቁና በሀገር አቀፍ ደረጃም ተጠቃሽ ናቸው።

ከጤና ተቋማት አንፃር በዞኑ አንድ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፣ አንድ የግል ጤና ጣቢያ እና 15 የመንግስት ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 228 የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የሚገኙ ሲሆን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን እያሳለጡ ይገኛሉ።

ከትምህርት ተቋማት አኳያ በዞኑ 91 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ 100 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 18 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቴፒ ግቢ  እንዲሁም የቴፒ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ጨምሮ 3 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በዞኑ የሚገኙ በመሆናቸው በትምህርቱ ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

 ከመሠረተ ልማት አንፃርም በዞኑ በሶስት አቅጣጫ ማለትም ማሻ-ቴፒ፣ ከሚዛን ቴፒ እና ከሺሽንዳ- ቴፒ በአጠቃላይ ከ2 00 ኪ.ሜ በላይ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በፌዴራል መንግስት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በክልል፣ በዞንና በህብረተሰብ ተሳትፎ ብዙ ኪሎ ሜትር መንገዶችና ድልድዮች እየተገነቡ ይገኛል።

የሸካ ዞን ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት የሚሆኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች የሚገኝበት ሲሆን ጋንዶቺ የተራራ ላይ ሀይቅ ፣ጋሀማዎ ፏፏቴ፣ ዱሻ ዋሻ፣ አጫ ፏፏቴ፣ ዱከቺ ፏፏቴን ጨምሮ በርካታ መስህቦች ይገኙበታል።

በዞኑ የሚገኙ ነባር ብሐረሰቦች ያልተነኩና ያልተበረዙ ትውፊትና ቱባ ባህሎች ዛሬም ድረስ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል።

ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንፃርም በተለይ በሸካ ዞን ዋና መቀመጫና የክልሉ ብዝሃ ዋና ከተማ በሆነችው ቴፒ ላይ የሆቴል ግንባታ በብዛት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ቴፒ ከተማ የመሬት አቀማመጧ ምቹና በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ በከተማዋ በኢኮ ቱሪዝም፣ በአግሮ ቱሪዝምና በመሳሰሉት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የተመቸ እምቅ አቅም ያላት ከተማ ነች። የዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ለቱሪዝምና ለሌሎች  የኢንቨስትመንት ዘርፎች ምቹ ናቸው።

ዞኑ የተረጋጋ ሰላም የሰፈነበት ዞን በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋትና በተደራሽነቱ እያደገ የሚገኝ እና ሰፊ መሰረተ ልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ዞን ነው።

በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የዞኑ የቱሪስት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እየመጣ ሲሆን ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎችን ፍላጎት ለማሟላት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥራትና በብዛት በመገንባት ላይ የሚገኝ ዞን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *