



የአላየሁ መላኩ አትሌቲክስ ክለብ ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት የ5 ኪሎሜትር ህዝባዊ የጎዳና ላይ ሩጫ በገዋታ ወረዳተካሂዷል ።
“አኩሪ አትሌቶችን በማፍራት የሀገራችንን ለውጥ እናረጋግጣለን ” በሚል መሪ ቃል በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ በሂንጊዶ ከተማ በተደረገው የጎዳና ላይ 5 ኪሎሜትር ሩጫ ከ300 በላይ ወንዶችና ሴቶች ተሳትፈዋል ።
በመርሃግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የወረዳው ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ሀይሌ ክለቡ በተሳተፈባቸው የተለያዩ ውድድሮች ውጤታማ እየሆነ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል ።
ክለቡ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል የወረዳው አስተዳደር ለልምምድ 1.5 ሄክታር መሬት ለክለቡ መስጠቱን በመግለጽ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአላዩ መላኩ አትሌቲክስ ክለብ ባለቤት ሃምሳ አለቃ አላዩ መላኩ 38 አትሌቲክሶችን በመያዝ ክለቡ መቋቋሙን ተናግረዋል ።
አሁን ላይ በማስልጠኛ ማዕከሉ 25 ሰልጣኝ አትሌቲክሶች እንደሚገኙና በግል ሀብታቸውን ኢንቨስት በማድረግ በዞን፣በክልልና በሀገር አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ በማድረግ ክለቡ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል ።
ክለቡ ሀገር አቀፍ ውድድሮችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦሎምፒክ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት በ3 ዓመታት ውስጥ በትኩረት ለመስራት ዕቅድ መያዛቸውን በዕለቱ ተናግረዋል ።
የካፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ተወካይ አቶ ሀረሩ ወርቁ “ይቻላል ” የሚለውን ሀሳብ በተግባር ያረጋገጠ ክለብ ስለመሆኑ ተናግረዋል ።
በዞኑ ብቸኛ ክለብ መሆኑን በመግለጽ አልሚ ባለሀብቶች የአላየሁ መላኩን ፈለግ በመከተልም በስፖርቱ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ።
የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ሀይሌ በበኩላቸው ክለቡን የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ቁሳቁሶች መደገፉን ገልጸዋል።
ክለቡ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ በተለያዩ ውድድሮችና ስልጠናዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ዘካርያስ ተናግረዋል ።
የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ በአላየሁ አትሌቲክስ ክለብ ሀገር የሚያስጠሩ ስፖርተኞች መፍለቂያ ተስፋ የተጣለበት ክለብ ስለመሆኑም ተናግረዋል ።
በክልሉ ስፖርት ከመዝናኛነት ባለፈ በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው እየጎላ መምጣቱንም አቶ አህመዲን ተናግረዋል ።
ስፖርት ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያወሱት አቶ አህመዲን አወል የአላየሁ መላኩ አትሌቲክስ ክለብ በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ ሂንጊዶ ቀበሌ የሚገኘው የአላየሁ መላኩ አትሌቲክስ ክለብ ህዝባዊ መሠረት ያገኘ ሞዴል ክለብ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ክለቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የቀበሌው አስተዳደር ፣የዞንና የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም አቶ አህመዲን አስታውሰዋል።
ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በዕለቱም የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች አካላት ክለቡን ለማጠናከር በተደረገው የገቢ ማሰባሰብ ስራ ከተለያዩ አካላት ከ275 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለክለቡ ተደርጓል።
ዛሬ በተደረገው የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ለአሸናፊዎች የሜዳሊያ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ክለቡ ለደረሰበት ደረጃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የሰርተፊኬት አሰጣጥ ስነስርዓት በማድረግ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
በታጠቅ አበበ
