ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ።

Spread the love

የመኧን አርብቶ አደር ማህበረሰብ ከኮንታና አጎራባች ህዝቦች ጋር የይቅርታና የእርቅ ስነ ስርዓት በኮይሻ ከተማ ተካሂዷል ።

በህብረተሰቡ ዘንድ ዘልቆ የቆየውን ተቃርኖ ለመፍታት በመኧን ማህበረሰብ ባህላዊ የእርቅና የይቅርታ ስነስርዓት (ታራይ) በመፈጸም ተከናውኗል ።

የእርቅና የይቅርታ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በመኧንና ኮንታ ኮይሻ ህብረተሰብ ዘንድ የቆየውን ቁርሾ ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ብርቱ ጥረቶችን አድርጓል ብለዋል።

በህብረተሰቦች መካከል ተፈጽመው የነበሩ ትንኮሳና ግጭቶች ቀላል እንዳልነበሩም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።

ግጭቶችንና ትንኮሳዎችን የሚያባብሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንም ማስቀረት ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

የአካባቢውን ህብረተሰብ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ መስተጋብሮች በማስተሳሰር ሰላምና ልማትን በማስቀጠል ብልጽግናን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።

ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎች ፣የጎሳ መሪዎች ትኩረት በመስጠት ሊሰሩም ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ይቅርታና እርቅ መደረጉ ለዘመናት የቆየውን በህዝቦች መካከል የነበረዉ ቁርሾ ተደምስሶ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጎለብት አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።

ዛሬ የተፈጸመው የይቅርታና እርቅ ስነ ስርዓት የእርስ በርስ መተማመንን በህብረተሰቡ ዘንድ መፍጠሩንም አቶ አንድነት ተናግረዋል ።

የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ከቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት (LLRP) ጋር በመተባበርም የእርቅና የይቅርታ ፕሮግራሙ መደረጉን ተናግረዋል ።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚስተዋለውን ግጭትና ትንኮሳ ለመከላከል የመሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲሰሩ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ተወካይ አቶ በቀለ ሎኮሮማ በዕለቱም ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በኦሞ ቀጠና አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች በባህልና በቋንቋ የተሳሰሩ በመሆናቸው ችግሮችን በመተባበርና በመቀናጀት እንፈታለን ሲሉ ተናግረዋል ።

በመኧን አርብቶ አደርና በኮንታ ኮይሻ አካባቢ ነዋሪዎች የነበረውን የዘመናት ቁርሾ ለመቅረፍ በባህላዊ የእርቅ ስነስርዓት መፈጸሙ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን የምዕራብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ ተናግረዋል ።

በመኧን ማህበረሰብ በኩል ለተፈጸመው በደል የኮንታ ኮይሻ ነዋሪዎች ላሳዩት ጨዋነት የተሞላው ይቅርታ ለአካባቢው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ቃል መግባታቸውን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል ።

የኮንታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸውም ከይቅርታና እርቅ ማግስት ዳግም ችግሮች እንዳያገረሹ ህብረተሰቡን ወደ ልማት የማስገባት ስራዎችን በመተባበር እንሰራለን ብለዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደመላሽ ንጉሴም ይቅርታ እና እርቀ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *