የቴፒ-ሚዛን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በሚቀጥለው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘው እና የቤንች ሸኮን እና የሸካ ዞኖችን የሚያገናኝ የቴፒ-ሚዛን 47.87 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በቀጣዩ በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት ፣ የማፋሰሻ ፣ የስትራክቸር ፣ የሰብ ቤዝ እና የቤዝ ኮርስ ንጣፍ እንዲሁም 25 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን እያከናወነ የሚገኘው ቻይና ግዞባ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር (CGGC) የተባለ የቻይና የስራ ተቋራጭ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራው ደግሞ ፕሮሚነንት ኢንጂነሪንግ ሶሉሽንስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በሚባል አማካሪ ድርጅት አማካኝነት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ለግንባታው ማስፈጸሚያ የሚውለውን 1,276,922,787 (አንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሰማንያ ሰባት) ብር በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው ።

አሁን ላይ የስራ ተቋራጩ ከአጠቃላይ ስራው 31.6 ኪሎ ሜትር ወይም 66 በመቶውን ያጠናቀቀ ሲሆን የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራዎችም በሚቀጥለው በጀት አመት (2018 ዓ.ም) ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል፡፡ እቅዱን ከግብ ለማድረስም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለድረሻ አካላት ጋር በተዋረድ ተቀናጅቶ እየሰራ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የቤንች ሸኮን እና የሸካ ዞኖችን የሚያገናኝ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው እንደ ቡና ፣ ሙዝ ፣ አቮካዶ ፣ ማር ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ፣ ቁንዶ በርበሬ እና ኮረሪማ እንዲሁም ፍራፍሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረቱ በመሆኑ እነዚህ ምርቶች በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲደረሱ በማስቻል ከፍተኛ ማህበራዊ እና አኮኖሚያዊ አስተዋጽኦን ያበረክታል፡፡

በተጨማሪም መንገዱ ሁለቱን ዞኖችን የሚያገናኝ ከመሆኑም ባሻገር በወረዳና በከተማ አስተዳደር ደረጃም የቴፒ ከተማ አስተዳደርን ፣ የኪ ወረዳን ፣ ሸኮ ከተማ አስተዳደርን ፣ ሸኮ ወረዳ እና ሚዛን አማን ከተማ አስተዳደርን በቅርበት በማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራቸውን ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ ይታመናል፡፡

መረጃው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *