“ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እያደረጉ ያሉ ኃይሎችን መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል።”፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

Spread the love

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፤ ሰላም ሁሌም የሚገነባና ተከታታይ ስራ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሚገባትን ሰላም እንዳልያዘች ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው ሰርተው እንዳይገቡ እያደረጉ ያሉ ሀይሎችን በተባበረ ክንድ መልክ ማስያዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ጥይት ባይተኮስም የሰውን ልጅ እንቅልፍ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተው፤ ሰላም ሁሌም አንጻራዊ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡ ጊዜ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የነበሩ ግጭቶች መፈናቀሎችና የዜጎች ህይወት መጥፋት በመላው ሀገሪቱ በመጣው አንጻራዊ ሰላም መቆም ችሏል ብለዋል፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዳሴው ግድብ እንዳይሰራ ከውጭ ሀገር ሰልጥነው የመጡ ዜጎችንም ወደሰላማዊ መንገድ መመለስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ያለው ሰላም ፍጹም ባይሆንም አንዴ ሰላም የለም የሚለውን ሀሳብ ሰው ጭንቅላቱ ውስጥ ስላስገባ ሰላምን በንጽጽር ለማየት ይቸገራል፤ ይህ ባይሆን ግብርናው፣ ኢንዱስትሪው፣ ማዕድኑና ሌላውም ዘርፍ ልያድግ አይችልም ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም ግጭቶችን ተያይዞ የተፈናቀሉ ዜጎች ቢመለሱም የቀሩ እንዳሉ በመገንዘብ ለተሰራው ስራ እውቅና በመስጠት እንሰራበታለን ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *