የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በሁለት ወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚዲያ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫው የክልላችን ህዝብ የጤና ስጋት የሆነው ወቅታዊ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት እና ከጥር 23/2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የሚከናወነው የተፋሰስ ንቅናቄ ላይ ያተኮረ ነው።
መግለጫ የሰጡት የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ በክልሉ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ከአካባቢ ወደ አካባቢ የበሽታው መጠን ቢለያይም በሁሉም ዞኖች እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የወባ ስርጭት የተመዘገበባቸው አካባቢዎች በቅደም ተከተል ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ሸካ ዞኖች ሲሆኑ ደቡብ ቤንች፣ ሜኤንት ጎሊዲያና ኮንታ ኮይሻ ወረዳዎች እንዲሁም ሚዛን አማን እና ቴፒ ከተማ አስተዳደሮች በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ ወ/ሮ በረከት ጠቅሰዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ ወባን ከተመረመሩት 5 መቶ 41 ሺ 932 ሰዎች መካከል 3 መቶ 11 ሺ 428 ሰዎች የወባ በሽታ የተገነባቸው ሲሆን በወባ የመያዝ ምጣኔ 57.5 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
ወረርሽኙ ለህዝቡ የጤና ስጋት ከመሆን ባለፈም በማህበራዊና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያስከትል ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደ ክልል በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ወ/ሮ በረከት ተናግረዋል።
በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበር ለ50 ወረዳዎች፣7ሺ 634 ኪሎግራም ቤት ለቤት የሚረጭ ኬሚካል፣ የወባ ጫና ባለባቸው 54 ወረዳዎች 2ሺህ 185 ሊትር የወባ ትንኝ እጭ መግደያ ኬሚካል ክፍፍል ተደርጓል።
እንዲሁም ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የወባ መከላከየ ግብዓቶች ለምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮና ኮንታ ዞኖች እንደተሰራጩና ህዝቡ ከበሽታው ራሱን እንዲብቅ የአጎበር አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውን ወ/ሮ በረከት ጠቅሰዋል።
እንደ ወ/ሮ በረከት ኢዮብ ገለጻ በክልሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ጋር የህብረተሰብ ንቃተ ጤና ለመጨመር በክልሉ ጤና ቢሮ በኩል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ስለ ወባ በሽታ ወቅታዊ መረጃ ተደራሽነትን በማረጋገጥ የመከላከል ግንዛቤ ሥራዎት እየተሰራ ይገኛሉ።
የወባ ወረርሽን የመከላከል ሥራ ከክልል ጀምሮ በርካታ አመራር የተሳተፈበት ግብረ ኃይል መቋቋሙን፣በሽታው በስፋት ጉዳት እያደረሰ ባለባቸዉ ዞኖች የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን፣ህገ ወጥ የመድሃኒት ዝዉውር ላይ ህግ የማስከበር ዕርምጃ መጀመሩን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
የአካባቢዉን ንጽህና መጠበቅ፤ኬሚካል የተነከረ የአልጋ አጎበር ሁልጊዜ መጠቀም፣ዉሃ ያቆሩ ስፍራዎችን ሁል ጊዜ ማዳፈንና ማፋሰስ ከህብረተሰቡ ስለሚጠበቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ /ሮ በረከት ጥሪ አቅርበው ሚዲያዎችም ለህብረተሰቡ ስለበሽታው አስከፊነት በተለያዩ ዝግጅቶች የመከላከል መንገዶች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሌላው በክልሉ ከጥር 20/2016 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ በርካታ ኩነቶች እንደሚኖሩ ያነሱት ኃላፊዋ ጥር 23 ክልላዊ የተፋሰስ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት በኮንታ ዞን እንደሚካሄድ በመግለጫቸው አስታውቋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባለፈ በክልላችን የሚገኙ ግቤ 3 እና ኮይሻ የሃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የምንወጣው ድርብ ሃላፊነት ነው ያሉት ኃላፊዋ ከይፋዊ ጀማሮ በተለዩ ሁሉም አካባቢዎች ስራው በግለት እንዲቀጥል ህብረተሰባችን በጋራ የመስራት ልማዱን አጠናክሮ የዘርፉ ባለሙያዎች በሚመሩት መንገድ የዘመቻውን ስራ ግብ ሊያሳኩት ይገባል ብለዋል።
ሚዲያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገርም ህዝቡ በተለይም የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የማነቃቃት ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በፍቅር ከበደ
