አረንጓዴዉ ወርቃችን..!

Spread the love

የቡና ምርት ለማሳደግ አዲስ ተከላ ማሳደግ እና ምርት ማሻሻያ ፓኬጅ መተግበር ወሳኝ ነው፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ምርት የተቀነሰባቸው የቡና ማሳዎችን በጉንዳላና በነቅሎ መትከል የማደስ ስራ ሌላኛው ምርት የማሻሻያ ተግባር ነው።

የቡና ግብይት ስርዓት ለማሳደግ ምርት ዝግጅትና ግብይት ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ የቡና ጥራት ጉድለት ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት በመፈጸም ጥራት ያለው የቡና ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ አስፈላጊ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቡና አምራች እና ላኪ ሀገሮች አንዷ ነች።በሀገርቱ ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ በቡና ምርትና ግብይት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡና አምራች ብቻ ሳይሆን መገናኛም ነው።

ክልሉ በቡና ምርትና ምርታማነት በኩል በሀገር አቀፉ ደረጃ ግንባር ቀደም እንዲሆን ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ይገኛል።

አቶ አስራት መኩሪያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ የቡና ዘርፍን ለማዘመን ከመሬት ማስፋት ጀምሮ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጊ ይገኛሉ።

የባለስልጣን መስሪያቤቱ በዋናነት የቡና ምርት ለማሳደግ አዲስ ተከላ ማሳደግ እና ምርት ማሻሻያ ፓኬጅ መተግበር ወሳኝ በመሆኑ ለዚህም በርካታ ስራዎች እየሰሩ መሆኑን አቶ አስራት አመልክተዋል።

የተሻሻሉ በሽታን መቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ ምርታማ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን ከታወቀ ከቡና ዘር ምንጭ የማዘጋጀት፣ የማሰራጨትና የችግኝ ዝግጅት ስራዎች ዋነኛ ተግባራት ናቸዉ ስሉም አቶ አስራት አክለዋል።

የምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጅ ትግበራ የአረም፣ የኩትኳቶ እንዲሁም ያረጀና በተለያዩ ምክንያቶች ምርት የቀነሰ ማሳ በጉንደላና በነቅሎ መትከል የማደስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በቡና ማሳ ላይ አፈር ለምነትን የሚያሻሽሉ የኮምፖስት ዝግጅትና አጠቃቀም አጠቃላይ ምርታማነትን የሚጨመሩ ዝርዝር ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸዉን ነዉ አቶ አስራት የገለጹት።

ምርት ዝግጅትና ግብይት ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ የቡና ጥራት ጉድለት ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም ጥራት ያለው የቡና ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መሥሪያቤቱ በ2016 በጀት ዓመት 54 ሺህ 1 መቶ ኪሎ ግራም የቡና ዘር የተለያዩ ምንጮችን በመጠቀም አዘጋጅቶ ለማቅረብ ያቀደ ሲሆን እስከአሁን ከ55ሺህ በላይ ኪሎግራም የቡና ዘር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ክልሉ ከራሱ አልፎ ለሲዳማ፣ ለደቡብ ኢትዮጵያና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ከ18ሺህ ኪሎግራም በላይ የቡና ዘር በተያዘው በጀት ዓመት ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ እንደሀገር የተጣለበትን ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አቶ አስራት ገልጸዋል።

በክልሉ ከመስከረም እስከ ታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ በ2ኛ ዙር ከሚያዝያ ወር እስከ ቀጣይ ክረምት የዝናብ ወራትን በመጠቀም አየር ንብረትና ስነምህዳርን ተከትሎ የቡና ዘር የማፍሰስ ስራ እየተሠራ መሆኑን ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ በ2016 በ1ኛ ዙር 13 ሺህ ኪሎግራም የቡና ዘር ለማፍሰስ ታቅዶ እስካሁን ከ8 ሺህ ኪሎግራም በላይ የቡና ዘር መፍሰሱን ተናግረዋል።

በክልላችን ለማዕከላዊና ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የቡና ምርት መጠን እንዲጨምር በበጀት ዓመቱ 67ሺህ 348 ቶን የታጠበና ያልታጠበ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ግብ ተጥሎ እየተሰራም ነዉ ያሉት አቶ አስራት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ 22 ሺህ 3 መቶ ቶን ምርት ለማቅረብ ታቅዶ እስከአሁን 20 ሺ 3 መቶ ቶን መቅረቡን ገልጸዋል።

በክልሉ 249 የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች አሉ።

በአጠቃላይ በግብይት ወቅት የሚስተዋሉ የህገወጥ ስራዎችን የመቆጣጠርና የመከላከል ስራ ይሰራል ሲሉ አቶ አስራት ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *