በ2017 በጀት ዓመት በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ተናገሩ ፡፡

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በታርጫ ከተማ ተጀምሯል ፡፡

ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወንድሙ ኩርታ በጉባኤው መክፈቻ እንደተናገሩት ባለፉት የበጀት ዓመት ምክርቤቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠዉን ሀላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በህገ-መንግስትና በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ የተሰጠዉን ተግባርና በበጀት አመቱ ያቀደዉን እንዲያሳካ በርካታ የአስፈጻሚ ተቋማትና የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ከምክር ቤቱ ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት ዉጤት እንዲመዘገብ አድርገዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የታቀዱ ተግባራትን ለማከናወን እንዲያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ከኦዲት ግኝቶች አንጻር ምክር ቤቱንና የምክር ቤቱን ኦዲት አስመላሽ ግብረ-ሀይል በማገዝ በኦዲት ግኝት አመላለስ ላይ ግብረ ሀይሉ የእቅዱን 75% እንዲያስፈጽም አስችሏል ብለዋል ፡፡

በታችኛዉ ም/ቤቶቻችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በበርካታ ዘርፎች ማለትም በጉባኤ አፈጻጸም፣ በጋራ ምክክር ፎረም፣የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮች መፈጠር፣ በኦዲት ግኝት ላይ ምላሽ እንዲሰጥ በግብረ ሀይል ተግባሩን መምራት ላይ መሻሻሎች መታየታቸዉ በጥንካሬ የሚገለጽ ተግባር ነው ብለዋል ፡፡

በጀት ዓመቱ በተለይ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ተንከባሎ የቆዩ ካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ ዉጤት ለማምጣት የክልሉ መንግስት ስፊ ጥረት በማድረግ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነም ተናግረዋል ፡፡

የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ምክር ቤቱ በልዩ ሁኔታ ለቀጣይ በጀት ዓመት ትኩረት እንዲሰጣቸዉ ከለያቸዉ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ግብርና ቢሮ ካለፉት ዓመታት የተለየ ለዉጥ በሁሉም ዘርፍ ለማምጣትና ሀገራዊ ኢንሼቲቮችን ለማሳካት ያደረገዉ ጥረት እጅግ በጣም የሚበረታ መሆኑንም ገልጸዋል ፡፡

በተለይ የቡና አብቃይ አካባቢዎች ላይ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል በግብርና ቢሮ በኩል የተጀመሩ በርካታ ተስፋ ሰጪ ተግባራት አሁንም ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል ፡፡

ህግ ማስከበርና በገጠር መሬት መጠቀሚያ አዋጅ መሰረት የአርሶ አደርና የኢንቨስትመንት መሬቶች ላይ ገቢን በአግባቡ መምራትላይ በታችኞች መዋቅሮች ዉስንነቶች መኖራቸውንና ልዩ ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል ፡፡

የትምህርት ቤትና የጤና ጣቢያዎች ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ የቅንጅት ጉድለቶችንና የሚሰበሰቡ ገቢዎች የፋይናንስ ስርዓቱን የተከተለ እንዲሆን ማስቻልም ይገባል ብለዋል ፡፡

ከጤና አንጻር የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል የተጀመሩ ቅንጅታዊ ስራዎችን ይበልጥ ማሳለጥ፣ከትምህርት አንጻር የተጀመረዉን የትምህርት ለትዉልድ ንቅናቄን በማጠናከር የት/ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስራዎች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሀላፊነታቸዉን በአግባቡ እንዲወጡም አፈ ጉባኤው ጠይቀዋል ፡፡

ከዳኝነት ስራዎች አንጻር በተለይ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸዉ አካባቢዎች ከታቸኛዉ መዋቅሮች ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት ህዝቡ በአቅራቢያዉ የዳኝነት አገልግሎት እንዲያገኝ ምድብ ችሎቶችን ተደራሽ ማድረግና በቁሳቁስና በሰዉ ሀይል ማደራጀት ይገባልም ብለዋል ፡፡

የክልሉ ም/ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ከሐምሌ 14 /2017 ዓ/ም ጀምሮ ከ2-3 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑንም አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ገልጸዋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *